አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 13፣2012

በሀገራችን በየጊዜው በሚከሰቱ የሀይማኖት ተቋማትን የማቃጠል እኩይ ተግባር ሲፈጸም የሀገራችን ሚዲያዎች የመደባበቅና ወገንተኝነት እንደሚስተዋልባቸውና ሀገራዊ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የማንነትና ወሰን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ አብራርተዋል፡፡

የሚዲያዎች አቋም ብዙ አይነትና የሚያሳዝን ነው የሚሉት ኡስታዙ ሽፋን ያልሰጡ ሚዲያዎችን ጨምሮ የተዛባ መረጃ በማስተላለፍና በገለልተኝነት ሚናቸውን የማይወጡ ሚዲያዎች እንደሌሉ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ የሀገራችን ሚዲያዎች ከመንግስት ጋር የቀጥታ ቁርኝት አላቸው የሚሉት ኡስታዝ አቡበከር አሁን ባለው ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሚዲያዎች ተሰጣቸውን ነጻነት በመጠቀም ተአማኒነት ያለው ወቅታዊና ገለልተኛ መረጃ ሊሰጡ እንደሚገባ ኡስታዝ ኡቡበከር አሳስበዋል፡፡

አሁን ላይ ለሚከሰቱ የቤተ እምነት ማቃጠል ችግሮች ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሀይማኖት ተቋማት ሀላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ኡስታዝ አቡበከር የገለጹ ሲሆን በምስራቅ ጎጃም ሞጣ የተደረገውን የመስጂድ ማቃጠል ተግባር የሀገሪቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ማህበረሰቡ አውግዟል፡፡