አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 13፣2012

ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) የአቋም መግጫ የሰጠ ሲሆን የዎላይታ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብት በኢትዮጵያ ህገ-መንግሰት

መሰረት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ባሉት መንግሰታዊ መዋቅሮች ሙሉ ይሁንታ አግኝቶና በሙሉ ድምጽ የጸደቀዉን የደቡብ ክልል ምክር ሕዝበ-ዉሳኔ እንዲያደረጅ ከመላኩም ባሻገር የሕዝብ ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝ በተለያዩ ጊዜያት የተጠየቀ ቢሆንም ባልተጻፈ ህግ በአምባገነናዊ አካሄድ ምላሹ ተከልክሏል ሲል አትቷል፡፡

ግናበሩ ሕዝቡ ድምጹን እንዳያሰማ በታህሳስ 10 2012 ህገ-ወጥ በሆነ ኮማንድ ፖስት የሕዝብ ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ታፍኖል ያለ ሲሆን በኢትዮጵያ ዉስጥ የዲሞክራሲ ጉዞ ላይ የዎላይታን ሕዝብ ባጋጠመዉ ህገ-መንግስት ጥሰት ዎሕዴግ ገዥ-መንግሰትን ይኮንናል ሲል አስረድቷል፡፡

መንግስት የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ የህገ-መንግስቱ ባለቤት የሆነዉ የዎላይታ ሕዝብ በታህሳስ 10 ያደረገዉን የክልል እንሁን እወጃ ዎሕዴግ እዉቅና እንደሚሰጥ ጠቅሶ ቀሪዉን ሥራ የዞን መንግስት ከሕዝብ ጎን በመቆም ከ2012  ምርጫ በፊት መስመር እንዲያስይዝ አሳስቧል፡፡

ዎህዴግ የፌደራል መንግሰቱ የደቡብ ክልል መንግስትን እጅ በመጠመዘዝ ኃይሉን በመቀማት መላዉን በደቡብ አቅጣጫ የሰየመዉን ሕዝብ ሥልጣን አልባ በማድረግ አሃዳዊ አገዛዙን በገሃድ አዉጇል በማለት የኮነነ ሲሆን ያለአግባብ ሥልጣንን የቀማዉ መንግስት የሕዝብ ሥልጣኑን እንዲመልስ በተለያዩ መዋቅሮች በኩል የሚደረጉ ትግሎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ግንባሩ የዎላይታ ህዝብ መብት ተሟጋች እና የዎብን ፓርቲ አመራር የሆነዉ አቶ አንዱዓለም ታደሰ ባራታ የታሰረበትን ሁኔታ በመፈተሸ ይህ የዲሞክራሲን ሂደት የሚያጨልም የኢሕአዴጋዊ ጠልፎ የመጣል ያረጀ የፖለቲካዊ ሴራና ስህተት ነው በማለት በአስቸኳይ እንዲፈታ ይጠይቃል፡፡

መግለጫው አክሎም በአጠቃላይ በዎላይታ ዬላጋዎች (ወጣቶች)፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በተለያዩ ቦታ ባሉት ዎላይታዎች ላይ እየተደረገ ያለዉ ወከባ ትግላችን የሚያጠነክር እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ ባለመሆኑ ሁሉም ዎላይታዎች ባሉበት ቦታ ሆነዉ አመጸ-አልባ ትግሎችን በመጠቀም በህልዉናቸዉ ላይ የተጋረጠዉን አደጋ ይታገላሉ ብሏል፡፡