ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ማክሰኞ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት የነበራቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ረቡዕ ታኅሣሥ 15 አዲስ አበባ ሲገቡ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ከ20 ዓመት በላይ የዘለቀው የኢትዮ-ኤርትራ ፍጥጫ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት መቀየሩን ተከትሎ የሁለቱ አገራት መሪዎችና የባሕል ቡድኖች ተደጋጋሚ ጉብኝተን ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡

ይሁንና ሁለቱ አገራት ከፍተዋቸው የነበሯቸውን ድንበሮች ከዘጉም ከርመዋል፡፡

መንግሥታቱ ድንበሮቹ የተዘጉት የግንኙነት ሕጋዊ ማዕቀፎች እስኪዘጋጁ ነው ቢሉም የሕግ ማዕቀፎቹ እስካሁን ይፋ አልሆኑም፡፡

ይህን መነሻ የሚያደርጉ የፖለቲካ ተንታኞች የሁለቱ አገራት ዕርቅ ተቋማዊ ከመሆን ይልቅ በግለሰብ መሪዎች ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ ሲተቹት፤ የሮርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ደግሞ ለተፈጠረው እርቀ ሰላም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ማድረጉ የቅርብ ትውስታ ነው፡፡

ዶ/ር ዐቢይ ሽልማቱ እንዲያገኝ የተለየ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩላቸው የነበሩትን ኢሳያስ በቅርቡ እንደሚያገኟቸውና በሁለቱ አገራት ሰላም ዙሪያ እንደሚመክሩ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በመሆኑም ዛሬ የሰላም ጓዴ የሆኑትን ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂን እና የልዑካን ቡድናቸውን ሁለተኛ ቤታቸው ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን በደኅና መጡ እላለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ቆይቶ ሰላም እንዲመጣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተነግሯል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ በህወሀት እና ኤርትራን በሚመራው ፓርቲ (ህግደፍ) መሀል እርቀ-ሰላም ለማውረድ ያሰበ ጉዞ ሰኞ ወደ ኤርትራ ሊደረግ እንደሆነ ትላንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በህወሀት እና ህግደፍ መሀል ያለው ጥርጣሬ እና አለመግባባት ለኢትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም እንቅፋት መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡