አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 16፣2012 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራዊ ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ ባካሄዱት ውይይት ውስጣዊ ችግርን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

በትግራይና አማራ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ችግር አለመኖሩን ያመላከተው ውይይቱ በፖለቲከኞችና የማኅበራዊ ለውጥ አራማጆች የሚደረጉ አተካራዎች መኖራውንና እነዚህን በመለየት በውይይት መፍታት እንደሚገባ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ሠላም መጠበቅ እንዳለበት ያሳቡት የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ ‹‹ጠላት በሌለበት ቦታ ሰይፍ መማዘዝ አያስፈልግም›› ብለዋል

የመገናኛ ብዙኃን፣ ምሁራንና ማኅበራዊ አንቂዎች መቃቃር ላይ መሥራታቸውን አቁመው የጋራ እሴት ላይ እንዲሠሩም በመድረኩ ተጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ በመድረኩ የተገኘው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ  “ጀግና ለመባል ከፈለግን እርስ በርሳችን መገዳደል ሳይሆን አንዱ ሌላውን ለማዳን መኖር ስንችል ነው” ብሏል፡፡

እንደ ሻለቃ ሀይሌ ገለፃ ከዚህ በፊት በሀገራችን ገዳይን በቢህሎቻችን የማጀገንና የማሞጋገስ ልምድ እንዳለን ሁሉ አሁን ላይ ጀግና መባል ያለበት የህዝቦች ዋንኛ ጠላት የሆነውን ድህነትን በመዋጋት ለውጥ ያመጣ፣ የህዝቦች ሰላምና አብሮነትን ያጠናከረ እርሱ እውነተኛ ጀግና መባል መቻል አለበት ብሏል፡፡

ሻለቃ ሐይሌ አክሎም እኛ ኢትዮጵያዊያን መትጋት ያለብን ሀገርን ለውጠው ለዓለም መትረፍ የሚችሉ ሰዎችን ማፍራት ላይ መሆን መቻል አለበት እንጂ በትንሽ በትልቁ የምንነታረክና የምንጋጭ መሆን የለብንም ብሏል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በዚሁ ጊዜ በበኩላቸው እንዳሉት የአማራና ትግራይ ህዝቦች በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በደም የተጋመዱና አገር በመገንባትና በመጠበቅም ታሪካዊ አንድነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአብሮነትና የአንድነት አኩሪ ታሪካቸውን በማጠልሸት የፖለቲካ ትርፍ የሚሹ አካላት ህዝቦቹን ለማጋጨት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች በአጠቃላይ ትውልዱ “በትብብር ችግሩን ከወዲሁ ካልፈቱ የታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ” ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ።