አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 16፣2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሸይኽ ቃሲም ታጁዲን የአማራ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ሽፋን የሰጡበትን መንገድ ተችተዋል፡፡

ሸይኽ ቃሲም ታጁዲን በወቅቱ የተከሰተውን ነገር መዘገብ እንደ ቅስቀሳ ይቆጠራል የሚል ፍራቻ ከሆነ ጊዜው የማህበራዊ ሚዲያ በመሆኑ ለሁሉም በያለበት መድረሱ ስለማይቀር የመገናኛ ብዙሀን ተገቢና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሞጣ እና ሌሎች አካባቢዎች እንደዚህ አይነት እኩይ ክስተት ሊያጋጥም እንደሚችል በርካታ አመላካች ጥቆማዎችን ሸይኽ ቃሲም በማስረጃ አብራርተዋል፡፡

በሞጣ በደረሰው ቃጠሎ መንግስት መግለጫ ባለማውጣቱ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው መልካም ትብብር ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችን አድንቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በበኩላቸው በደረሰው ቃጠሎ መንግስት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸው ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ የክልሉ ፖሊስ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ከሞጣ ነዋሪ በላይ ለሞጣ የቀረበ ህዝብ የለም ያሉት ኮሚሽነሩ የደረሰውን ጥፋት በማስተጋባት ያልተገባ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ ጉዳዩ የማይመለከታቸው የሌሎች አካባቢዎች ህዝቦች ከቀስቃሽነትና እኩይ ድርጊታቸው በመቆጠብ ክልሉ በራሱ መንገድ እንዲወስን ነጻነት ሊሰጡት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡