አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 17፣2012

የዎላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ታፍኗል በሚል የዎላይታ ዞን ምክር ቤት ጉዳዩ ለሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዘለግ ያለ አቤቱታ አቅርቧል።

ዞኑ እንደዚህ አይነት አቤቱታ በኢትዮጵያ ታሪክ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን አቤቱታው የወላይታ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ በህገ መንግስቱ በተቀመጠለት የአንድ አመት ጊዜ ገደብ ፈጣን ምላሽ ሊሰጠው ሲገባ በጥናት እንመለሳለን እየተባለ ሲጓተት ቆይቷል ብሏል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት በጻፈው አቤቱታ የክልል መመስረት ጥያቄ በብሄር ብሄረሰቡ ወይም በህዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽ ሁፍ ለክልል ምክር ቤት ሲቀርብ ፣ጥያቄው የደረሰው የክልሉ ምክር ቤት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሄር ብሄረሰቡ ወይም ህዝቡ ሲደገፍ፣ የክልሉ ምክር ቤት ለጠየቀው ህዝብ ስልጣኑን ሲያስረክብና በህዝብ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን የክልልነት ጥያቄው በቀጥታ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚገባው ገልጧል፡፡

የወላይታ ህዝብ በ1983 ዓ.ም ራሱን ችሎ በክልልነት ተደራጅቶ እንደነበርና በኋላም ባልታወቀ ምክንያት ከደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተጨፍልቆ እንዲዋቀር መደረጉ የሚታወስ ነው ያለው አቤቱታው ህዝቡ ያለማቋረጥ ክልልነት ጥያቄን ሲያቀርብ ነበር ብሏል፡፡

የወላይታ ህዝብ ክልል የመመስረት ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጾ  የወላይታ ብሄር የራሱ ክልል ቢኖረው ለሀገሪቱ እድገትና ለውጥ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማመን የዞኑ ምክር ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ በሙሉ ድምጽ ተስማምቶበታል ሲል አብራርቷል፡፡