አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 17፣2012

ዛሬ ታህሳስ 17፣ 2012 በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በመስጅዶች ላይ የተፈጸመውን የማቃጠል ተግባር በማውገዝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ ሰልፍ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች የአማራ ክልል ደቡብና ሰሜን ወሎ ሙስሊሞች ድምጻቸውን ያሰሙበት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መዲና ደሴ ከተማን ጨምሮ በቦረና መካነሰላም ደጋን፤ ሀርቡና ባቲ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ወልዲያና መርሳ ከተሞች ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ከጁምዓ ሰላት በኋላ የተቃውሞ ድምጹን ያሰማው የአዲስ አበባ ከተማ ሙስሊም ማህበረሰብ ፒያሳ በሚገኘው ኑር መስጅድ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በአዲስ አበባ በአደባባይ ይደረጋል ስለተባለው ሰልፍ በሰጠው መግለጫ አንዳንድ ብዥታዎችን ማጥራት አስፈላጊ ነው በሚል ዛሬ በሰጠው መግለጫ የጋራ ነጥቦች እንዲወሰዱ አስገንዝቧል፡፡

በሞጣ የደረሰውን የሙስሊም ጠል ዘመቻ እና ጥቃት ለመቃወም በመላው አገሪቱ ሰልፍ እንደሚደረግ እና ይህም የሚደረገው ከመጅሊስ ጋር በህጋዊ መልኩ ፍቃድ በማውጣት እንደሚሆን ተወስኖ ለህዝብ እንዲነገር ተደርጎ ነበር ያለው ኮሚቴው ሰልፉ በመጅሊስ ፈቃድ እንዲካሄድ ሐሳቡን ያቀረበውም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው እንደነበር አስታውቋል።

ለዚህም ሲባል በመጅሊሱ እና በመፍትሄ አፋላላጊ ኮሚቴው መካከል በተደረገ ውይይት አጣሪ እና ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል ያለው መግለጫው ይህ ኮሚቴ ከተቋቋመ በኋላ ስብሰባዎች የተደረጉ ሲሆን በሚቀጥለው እሁድ በመላ አገሪቱ እና ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት በሚገኙባቸው አገራት የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ በኮሚቴው ውሳኔ ቢሰጥም ይህ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ ግን አፍራሽ ዓላማ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ስብሰባው ላይ ጣልቃ ገብተው ችግር በመፍጠር ኮሚቴው ላይ ጫና በማሳደር በድጋሚ የአዲስ አበባው የአደባባይ ሰልፍ ለአንድ ሳምንት እንዲራዘምና እስከ ታህሳስ 22 ድረስ ባለው የጊዜ ገደብ መጅሊሱ ከመንግስት ጋር ተነጋግሮ የሚያመጣው ምላሽ እንዲጠበቅ አስወስነዋል ብሏል።

በመጨረሻም በአደባባይ የሚደረገው ሰልፍ እስከ ታህሳስ 22 ተጠብቆ ከመጅሊሱ ጋር በጋራ እንደሚደረግና የመስጊዱ ተቃውሞ ግን ባለበት እንደሚቀጥል ተነጋግረው መለያየታቸውን ለአባይ ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።