አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 17፣2012

ባለፉት ዓመታት በስራቸው ላይ ፖለቲካዊ ጫና ይደርስባቸው እንደነበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓላማ አባላት ገለፁ፡፡

‹‹የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ›› በሚል ርዕስ የደህንነትና የፀጥታ አካላት አሠራርና ሪፎርምን አስመልክቶ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደው መድረክ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች አገሪቱ ችግር ውስጥ ስትገባ የፓርላማ አባላት ዝምተኛ ነበሩ፤ የመፍትሄ አካል መሆን ሲገባቸው እንዳለየ ሆነው ሲያልፉ ነበር የሚል ወቀሳ ሠንዝረዋል፡፡

ለተነሳው ወቀሳ በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ የምክር ቤቱ አባላት በወቅቱ ፖለቲካዊ ጫና ይረግባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሰላም ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ብርቱካን ሰብስቤ እንደተናገሩት፤ በወቅቱ የነበሩት አንዳንድ ህጎችና አዋጆች ከመጽደቃቸው በፊት በሚደረግ ምክክር ላይ ተቃውሞ ያደረገ የምክር ቤቱ አባል በልዩ ሁኔታ ይገመገም ነበር ብለዋል።

እንደ ወ/ሮ ብርቱካን ገለጻ፤ በተለይም የሊዝ አዋጁ ሲጸድቅ በነበረው ከፍተኛ ክርክር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀር ተጠርተው መጥተው ግምገማ ተካሂዶባቸዋል። አዋጁም በጉልበት እንዲጸድቅ ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የምክር ቤቱ አባላት ጫና ከነበረባቸው ለምን አይለቁም የሚል ጥያቄ የተሰነዘረ ሲሆን፤ ወ/ሮ ብርቱካን በሰጡት ምላሽ ያንን ለማድረግ ቢሞከር በሌላው አካል ላይ ይደርስ የነበረው እጣ በእኛ ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት ነበረብን ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደተናገሩት፤ ፖለቲካዊ ጫናው እስከ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድረስ የዘለቀ ነበር።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ ሌላው ስራ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ካቢኔያቸውን ነጻ ሆኖ የማዋቀር መብት እንኳን ተነፍገው እንደነበር አዲስ ዘመን ዘግቧል።