አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 23፣2012 ዓ.ም

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር፤ ዛሬ ሐሙስ ማለዳ  በታጠቁ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ተናገሩ።

የተከበሩ አቶ አብዱላሂ ለመንግሥት ሥራ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ ሳሉ መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ በየነ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ዛሬ ማለዳ 1፡30 ላይ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ቤንጓ አካባቢ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱም በመኪናው ውሰጥ የነበሩ አንድ ወንድና አንድ ሴት ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ኃላፊ በህክምና እርዳታ ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ገልፀዋል።

አቶ መለስ በቅርቡ አንድ የፖሊስ ኃላፊ በታጣቂዎች መገደላቸውን ገልፀው፣ ከክልሉ ተነስቶ አሮሚያ ክልልን የሚያቋርጠው መንገድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ስጋት የነበረበት መሆኑን አስታውሰዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥት ኃላፊዎችን ኢላማ አድርገው በታጣቂዎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ ስምንት ኃላፊዎች መገደላቸው ተነግሯል። በጥቃቱ ሌሎችም ሰዎች ሰለባ በመሆናቸው የሟቾች ቁጥር ከፍ ያለ ነው።

ኦነግ ሸኔ በአካባባው በሚፈፅማቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በአካባቢው ተቆርጦ መቆየቱን የገለፁት የጽ/ቤት ኃላፊው የችግሩ ስፋት ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ መሆኑ የፌደራል መንግስት የህግ የበላይነትን ሊያስከብር እንደሚገባም አቶ መለሠ በየነ ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው በአመራሮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ስለሚፈፀሙ ወደሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመሄድ ከአየር ትራንስፖርት ውጭ ሌሎች አማራጮች እንደሌሉም ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

የአቶ አብዱላሂን አስክሬን ለማምጣት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ቦታው ማቅነታቸውንም ገልፀዋል፡፡

በቅርቡም በአካባቢው በኦነግ ሸኔ በአንድ የፖሊስ አመራር ላይ ግድያ መፈፀሙ የሚታወስ ነው::