አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 30፣2012 ዓ.ም

አቶ ጀዋር የቀድሞው ኢህአዴግ በአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚመራ ነበር አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በአንድ ግለሰብ የበላይነት የሚመራ ነው ብለዋል፡፡

አሀዳዊነትን እንደ ማሳመኛ ለማድረግ ይሞክራሉ የሚሉት አቶ ጀዋር ያለፈው ኢህአዴግም ሆነ አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አምባ ገነናዊ ስርዓትን ለመገንባት ይፈልጋሉ ሲሉም ኮንነዋል፡፡

አቶ ጀዋር ህዝብ ነጻ፣ፍትሀዊ እና ፉክክር የተሞላበት ምርጫ እንዲያደርግ እድል እስካልተሰጠ ድረስ ህዝብና ሀገርን ማዳን አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ አምባገነናዊ ስርዓትን መገንባት ይፈልጋል የሚሉት አቶ ጀዋር አምባገነናዊ ስርዓትን ለመገንባት ከሚያስችሉ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ጠንካራ ማህበራዊ ድጋፍ፣ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት እና ጠንካራ የደህንነት አቅም አንጻር ግን ብልጽግና ሁለቱን እንኳን ማሟላት ስለማይችል አምባገነናዊ ስርዓት መመስረት አይችልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ጀዋር ገለጻ እነ ዶክተር አብይ የዴሞክራሲ ስርዓትን አለማመዱ የምንለው በቀጣዩ ምርጫ ኮሮጆ ካላሰረቁ፣የጸጥታ ሀይሉን አፍን ግደል አስፈራራ ካላሉት፣የምርጫ ቦርድን እጅ ጠምዝዘው አድሎአዊ አሰራርን ካላመጡ፣እንደ ማንኛውም ፓርቲ ተወዳድረውና ተፎካክረው ማሸነፍ ከቻሉ ፣ከተሸነፉ ደግሞ ያለምንም እፍረት ስልጣንን ለአሸናፊው አካል ማስረከብ ከቻሉ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጀዋር ጨምርውም በመጭው ምርጫ ከተሸነፍን ያገኘነውን ወንበር ይዘን ፓርላማ ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ ለመሆን ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን በተመለከተ ወቅቱ  የሽግግር በመሆኑና ከነበረችበት የቀድሞ ፖለቲካዊ አመለካከት በመነሳት በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተመረጠችበት ሂደት አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

በቅርቡ የኦሮሚያ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ኦፌኮን የተቀላቀሉት አቶ ጀዋር ወደ አገር ቤት ስመጣ ፍላጎት ባይኖረኝም የሽግግሩ መበላሸት ወደ ፓርቲነት እንድገባ አስገድዶኛል ብለዋል፡፡