አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 30፣2012 ዓ.ም

የደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በሞጣ ከተማ በመገኘት በቅርቡ ቃጠሎ ለደረሰባቸው መስጊዶች የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

የከተማ አስተዳደሩ የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ ዓለማየሁ እንደገለፁት ከባለሀብቶች፣ ከወጣት ማህበራት፣ ከእስልምናና ከክርስትና አባቶች፣ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የተውጣጡ ተወካዮች ትናንት ሞጣ በመገኘት 200 ሺህ ብር አበርክተዋል። ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ የሞጣ ከተማ አስተዳደር ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት 100 ሺህ ብር ዛሬ ገቢ ማድረጉን አቶ መንግስቱ አመልክተዋል፡፡

አገልግሎት ጽ/ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም ከ5 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የውኃ መስመሮችን ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ቡድን መሪው አስረድተዋል፡፡