አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 2፣2012 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ ዐዋጅን  አጽድቋል፡፡ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲሁም አጠቃቀም አስፈሪ በሆነ መልክ መስፋፋት ያስተዋሉ ወገኖች የሕጉን መውጣት ከመዘግየቱ በስተቀር በአዎንታ ተቀብለውታል፡፡

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው የሰብዓዊ ቀውሱን በአስቸጋሪ ደረጃ እንዳሳደገውም የሚታወስ ነው፡፡ እነሜንጫ፣ ገጀራ፣ ቀስት፣ ጦር፣ ሴንጢ እና የመሳሰሉት ባህላዊ መሣሪያዎች ሳይቀር ኢ- ሰብዓዊ በሆነ መልኩ ለሰዎች ጭፍጨፋ ውለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ሐተታ ክልከላው አርሶደሩ የሚጠቀምበትን መሣሪያዎች እንደማይመለከትና አርሶአደሮች ለማምረቻ መሣሪያነት የፈለጉትን ያህል መጠቀም እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱን አዋጅ የጦር መሳሪያ፣ ቀላል የጦር መሳሪያ፣ ትናንሽ የጦር መሳሪያ፣ ሙሉ አውቶማቲክ፣ ግማሽ አውቶማቲክና አውቶማቲክ ያልሆነ የጦር መሣሪያ ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም አስቀምጧል፡፡ ለዚህ አዋጅ በሚመች መልኩ አንዳንዶቹም ከአለምአቀፍ ትርጉማቸው ለየት ባለመልኩ ለመተርጎም ጥረት ተደርጓል፡፡

የጦር መሳሪያ ባይሆኑም የጦር መሳሪያን ያክል አደገኛ በመሆናቸው አጠቃቀማቸውን፣ ስርጭታቸውን እና የአመራረት ሂደቱን መቆጣጠርና በህግ አግባብ መግዛት አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳት ማድረሻ ዕቃዎችን በህጉ ውስጥ ለማካተት የተሞከረ ሲሆን በዚሁ መሠረት በስለታማነታቸው ምክንያት ወይም የኤሌክትሪክ ሀይል በመጠቀም ወይም መርዛማ በመሆናቸው ነው፡፡

በሰው አካልና ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ የሚችሉ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ጎራዴ፣ ሴንጢ፣ ጦር፣ ሜንጫ፣ቀስትና ተመሳሳይ መሳሪያዎችን እንዲሁም በእጅ የሚያዙ ቴዘር መሳሪያዎች፣ አስለቃሽ ጢስ፣ እና ተመሳሳይነት ያላቸውን ኬሚካሎች ጉዳት ማድረሻ እቃዎች በሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡