አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 2፣2012 ዓ.ም

አንዳንድ የምእራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች በአራቱም የኦሮሚያ ዞኖች በተለይ በምእራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ በመንግስትና ሸማቂዎች መካከል በሚደረገው የተኩስ ልውውጥ የህብረተሰቡ ሰላም ስጋት ላይ መውደቁን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አርብ ታህሳስ 24፣ 2012 አ.ም በምእራብና ቄለም ወለጋ ስልክና ኢንተርኔት በማቋረጥ መንግስት እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይበልጡኑ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያችን እና ሰላማችን ላይ አደጋ እንዲጋረጥ አድርጓል ብለዋል፡፡

ምእራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎች ላይ መንግስት የሃይል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ገልጸዋል፡፡

ወደ ምእራብ የሚገኙ ህዝቦች ችግር ውስጥ ናቸው እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ሃሰት ነው ያሉ ሲሆን በእርግጥ ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ሰቆቃ ውስጥ እንደነበር ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ሰላም እንዲሰፍን በሰላማዊ መንገድ መሞከሩን እና ይህ ግን ሳይቻል ሲቀር መንግስት በጸጥታ ሀይሉ አማካኝነት እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው የስልክ እና የኢንተርኔት መቋረጥ ግን ከእርምጃው ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታዬ ከታጣቂዎቹም ጋር ምንም እምንወያየው ነገር የለም የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝቡን ደህንነት ለማስከበር መንግስት ሃላፊነቱን ይወጣል፣ በምእራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ኮማንድ ፖስት የሚባል ነገርም የለም ያሉ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ የቦረና ፣ጉጂ ፣ምስራቅወለጋ፣ምእራብ ወለጋ፣ሆሮጉድሩ ወለጋ ፣ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቡር እና ቡኖ በደሌ በአሁኑ ወቅት በኮማንድ ፖስት ውስጥ የሚተዳደሩ አካባቢዎች በመደበኛ ስርአት ስር እንዲተዳደሩ ጠይቋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በምእራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ የ2012 ሃገር አቀፍ ምርጫ ጉዳይ ሲገልጹም ችግሩ የባሰባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት ሰላም በማስከበርና ሁሉንም ነገር በማስተካከል የሌሎቹንም የኦሮሚያ አካባቢዎች ለምርጫ የሚደረገው ዝግጅቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡