አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 2፣2012 ዓ.ም

ከሳምንታት በፊት ነበር አስራ ሰባት የሚደርሱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ የአማራ ተወላጆች በዩኒቨርሲቲው በነበረው አለመረጋጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ መንገድ ላይ እያ ሉ ነበር በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ አካባቢ መታገታቸው የተሰማው፡፡

ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች በመሆናቸው አሁን ላይ ተማሪዎቹ ያሉበት የጤና ሁኔታ በውል ስለማይታወቅ መንግስት በአፋጣኝ ተማሪዎችን ማስለቀቅ አለበት ሲሉ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ አዴኃን፣የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን፣የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ ጠይቀዋል ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ለአባይ ሚዲያ እንደገለጹት አሁን ላይ የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ መንግስት ማስለቀቅ አለበት ያሉ ሲሆን የሀገሪቱን ከፍተኛ የመንግስት ባለ ስልጣናት ሳይቀር በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያስጠይቃቸው ገልጸዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል ህዝብን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ተማሪዎችን ከገቡበት ችግር ሊያወጧቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ በበኩሉ የታገቱ ተማሪዎች ያለምንም የደህንነት ችግር መለቀቅ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ሞት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡