አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 2፣2012 ዓ.ም

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ላክዴር ላክባክ እንደገለፁት፤ የምክር ቤቱ አባላት ከታህሳስ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ከህዝብ ጋር ውይይት ጀምረዋል፡፡

አመራሩ ጠንካራ ሱፐርቪዥን ሥራ እያከናወነ ሲሆን በጅምር የቀሩ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ፣ ያልተጀመሩ ትኩረት እንዲሰጣቸው እና እየተሰሩ ያሉት ደግሞ መፋጠን በሚችሉበት ላይ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡

እንደ አቶ ላክዴር መግለጫ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በክልሉ በተለያዩ ወቅቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬያቸው እየተመለሱ ነው፡፡

ይሁንና ያልተሟሉ መሠረተ ልማቶች በመኖራቸው ሥራው የታሰበውን ያክል ስኬታማ አልሆነም፡፡

ከህዝብ ጋር በተደረገ ምክክር እንደ ክልል የመንገድ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ቴሌኮም እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ተደራሽነት በቂ ባለመሆኑ ጥያቄዎች በሰፊው ተነስተዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍተቶችን በመጠቀም የፀጥታ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ በተለይም የእርስ በእርስ ግጭት ዋነኛ ውስጣዊ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡

 ከውጭ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ጥቃት የሚያደርሱ የሙርሌ ጎሳዎች ስጋት ሆነዋል፡፡

ቀደም ሲል ከተከሰቱ ድንበር ዘለል ጥቃቶች 75 ከመቶ የሚሆነውን የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብቶበት መፍትሄ ተበጅቷል፡፡ የታገቱ ህፃናትም ወደቤተሰባቸው ተመልሰዋል፡፡

ይሁንና የተዘረፉ እንስሳት እስካሁን አልተመለሱም፡፡ ይህ ጉዳይ እስካሁን አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፤ በቀጣይ ችግሮች እንዳይከሰቱም ዳር ያሉ ወረዳ እና ቀበሌዎች ላይ በሰፊው እየተሰራ ነው፡፡

ይሁንና እነዚህ ጥያቄዎች በክልሉ አቅም ብቻ የሚመለሱ ባለመሆናቸው የፌዴራል መንግስት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አቶ ላክዴር ጠይቀዋል፡፡

እንደ አቶ ላክዴር ገለፃ፤ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያም ዝውውርም ከፍተኛ ስጋት ሆኗል፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው ችግር በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በጋምቤላ ክልል ላይ ጫና ፈጥሯል ይህንንም በመጠቀም አንዳንዶች ህገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርን ቢዝነስ አድርገውታል ብለዋል፡፡