አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 2፣2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ታህሳስ 27/2012 ዓ.ም ለህዝብ ባስተላለፈው መልዕክት ለኢዜማ ህጋዊ ዕውቅና ለመስጠት እንደወሰነ ገልጾ ውሳኔውን የሚቃወም አካል ካለ ተቃውሞውን እንዲያቀርብ በጠየቀው መሰረት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡

ኢዴፓ በተቃውሞው እንዳለው ኢዴፓ ከስሞ ከኢዜማ ጋር ተዋህዷል በማለት በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን በሀሰት ለህዝብ አሰራጭቷል ያለ ሲሆን ዶ/ር ጫኔ ከበደን ጨምሮ የቀድሞ የኢዴፓ አስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የነበሩ አራት ግለሰቦች የኢዜማ ከፍተኛ አመራር ሆነው ተመርጠዋል ብሏል፡፡

ሆኖም ግለሰቦቹ ከኢዴፓ አባልነት ሲነሱ የፓርቲውን ንብረቶች ሳያስረክቡና ክሊራንስ ሳይሰጣቸው ከፍተኛ አመራር ሆነው በመመረጣቸው የፓርቲያችንን ጥቅም ስለሚጎዳ ዕውቅናው ሊሰጠው አይገባም፡፡

ፓርቲው አክሎም በተለይ ዶ/ር ጫኔ ከበደ የኢዴፓን ህጋዊ ማህተም በመጠቀምና የኢዴፓ መሪ ነኝ በማለት ከምርጫ ቦርድ ጋር ደብዳቤ እየተፃፃፉ ይገኛሉ ሲል ገልጧል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) የድርጅት ክፍል ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ኢዜማ ግለሰቦችና ፓርቲዎች ፓርቲነታቸውን አክስመው የመሰረቱት ፓርቲ ነው ያሉ ሲሆን ፓርቲው ደግሞ ተቃውሞ ሊቀርብበት የሚችለው በስያሜውና በአርማው ነው እንጂ በግለሰብ ጉዳይ ተቃውሞ ሊቀርብበት አይገባም ብለዋል፡፡

ማንኛውም ግለሰብ ከአንዱ ፓርቲ ወጥቶ የሌላ ፓርቲ አባል የመሆን መብት አለው ያሉት አቶ ዋሲሁን ከለለቀቁበት ፓርቲ ክሊራንስ አምጥተዋል አላመጡም ብለን የምንጠይቅበት አግባብ ግን የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሃላፊው አክለውም የንብረት ጉዳይ ካለ ግለሰቦቹን ማናገርና ከነሱ ጋር መጨረስ ነው እንጂ ፓርቲው በዚህ ጉዳይ ዕውቅና የማግኘት መብቱ ሊገደብ አይገባም ብለዋል፡፡