“ከጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ ዘመቻ” አስተባባሪ ግብረሀይል የተሰጠ መግለጫ

እገታው በሽብር ድርጊት ሊፈረጅ ይገባል!!

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

ሰሞኑን ደሞ ሌላ ልብ የሚሰብር ዜና እየተሰማ ነው። ኦሮሚያ ውስጥ ታግተው የሚገኙት አስራ ሰባት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ለማንም ሰብአዊ ፍጡር የመንፈስ እረፍት የሚሰጥ አይደለም።

ይህ ድርጊት እየደረሰ ያለው በሀገራችን በኢትዮጲያ ውስጥ ነው። ወጣቶቻችን የታገቱት በጆሴፍ ኮኒው lRA ወይም በናይጄሪያው ቦኮሀራም አይደለም። ድርጊቱ የተፈፀመው በድንበር ዘለል የሙርሲ ጎሳ ታጣቂዎችም አይደለም። የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ሰለባዎችም ኢትዮጲያውያን ናቸው። እነሆ የዘር ፖለቲካ ሀገር በቀል አሸባሪዎችን ቀፍቅፎልናል። የልጆቻችን፣ የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ህይወት በነብሰ በላ አራዊቶቾ መዳፍ ውስጥ ገብቷል። አለመታደል ሆነና የነዚህ ንፁሀን ተማሪዎቻችን በህይወት መኖር የሚወሰነው በነዚሁ ሀገር በቀል አረመኔዎች መልካም ፈቃድ ሆኗል።

ይህ ድርጊት የጎሳ ፖለቲካ ያመጣብን መዘዝ ነው። ወጣቶቹ የታገቱት በብሄር ማንነታቸው ተነቅሰው ነው። ህግና ስርአትን ማስከበር በዋነኝነት የመንግስት ሀላፊነትና ግዴታ ነው። ህግ አስከባሪው አካል የአንድ ዘር ሶፍትዌር ተጭኖበት እያለ እንዴት ነው በሌሎች ብሄሮች አባላት ላይ ለሚፈፀም በደል ህጋዊ ምላሽ የሚሰጠው?? በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እኮ የወጣቶች ነብስ ባመፃ ሲነጠቅና የናቶች እምባ እንደ ጅረት ሲፈስ ወራቶች አልፈው፣ አመት አልፎ፣ አመታትን ልንቆጥር ዋዜማው ላይ ደርሰናል። ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በፌዴራል ስር እንደሚተዳደሩ በህግ ተደንግጎ ሳለ፣ ፌደራል ፖሊስ ህግ ለማስከበር ወደ ካሞፖሶች መላክ ከጀመረ ገና ወር እንኳን አልሞላውም። ማን ነበር ታዲያ ያ ሁሉ ግፍ በወጣቶቻችን ላይ ሲፈፀም በተቋማቱ አጠገብ ቅርብ ሆኖ የመንግስትን ህግ የማስከበር ግዴታ ተረክቦ የነበረው? መልሱ በዋነኛነትየክልል ልዩ ሀይል የሚባለሉት ናቸው።

በአሁኑ ሰአት እነዚህ ተማሪዎች የት ነው ያሉት? በህይወትስ አሉ? ካሉስ በምን ሁኔታ? መቼና ማን ነው ያገታቸው? እነማን ናቸው ታጋቾቹ? እስካሁንስ መንግስት ምን እያደረገ ነው? “ስለ እገታው መረጃ የለንም” የሚለው ስላቅ ይቅርና የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላት በወቅቱ ለህዝብ አላሳወቁም?

ውድ ወገኖች በነዚህ ወገኖቻችን ላይ ከታገቱበት ሰአት ጀምሮ ምን እየተፈፀመ እንደሆነ እስካሁን አይታወቅም። በህይወት ስለመኖራቸው የተረጋገጠ መረጃ የለም። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዛታቸው 30% በሆኑባት ኢትዮጲያ ከ80% በላይ እንስት ተማሪዎች ሲታገቱ እገታው ዘር ተኮር ብቻ ሳይሆን ፆታ ተኮር መሆኑም አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል። እየተኬደበት ያለው መንገድ ወደ ሀይማኖት ቀውስ እያጓጓዘን ወደ ፆታዊ ሰቆቃ እያሸጋገረን ይገኛል።ከታጋቾቹ የፆታ ተዋፅኦ አንፃር ስናሰላው ታጋቾቹ በህይወት አሉ ብለን እንኳን ብናስብ ሊደርስባቸው ከሚችለው አካላዊና መንፈሳዊ ሰቆቃ ሚዛን የሚደፋው ፆታዊ ጥቃቱ ነው። በህይወት ብናገኛቸው እንኳን መንፈሳዊው ሰቆቃው እስከ የህይወታቸው ማብቂያ ድረስ አብሯቸው ይኖራል። ላላስፈላጊ እርግዝናና ለህይወት ዘመን በሽታ የመጋለጣቸው እድላቸው ሰፊ ነው። እንደ ህዝብ የሚደርስብን ሀዘንና ብሄራዊ ውርደት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቤተሰብ ደረጃ ሊደርስ የሚችለውን መንፈሳዊ ድቀት ማሰብ በራሱ ህመሙ የበረታ ነው።

ስለዚህ መንግስት ዳተኛነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ የሚከተሉትን እንዲያደርግ አስተባባሪ ግብረሀይሉ በጥብቅ ያሳስባል

1- መንግስት በእገታው ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችን ለህዝብ እንዲያሳውቅ

2- በተቻለ መጠን የተማሪዎቹን ህይወት አደጋ ላይ ከሚጥል እርምጃ እንዲቆጠብ

3- በሰላማዊ መንገድ ታጋቾቹን ማስለቀቅ ካልተቻለ መንግስት የሚወስደው የሀይል እርምጃ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ ያገናዘበ እንዲሆን

4- የክልል ሀይሎች ከእርምጃው ዙሪያ እንዲርቁ እንዲያደርግ

5- የሽምግልና ጥረቶች በጎ ቢሆኑም ከተሞክሮ እንዳየነው ግን ለወንጀለኞች የወንድ በር የሚያሰጡ ናቸውና መንግስት በህግ ማስከበር ሂደት ያለውን አይተኬና ሉአላዊ ሚና እንዲያስከብር

6- ከዚህ ቀውስ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትና ቀውሱን ለማባባስ እየተንቀሳቀሱ ባሉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ

7- አጋቹ አካል በኢትዮጲያም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ እንዲደረግ የሚሉ ናቸው።

በዚሁ አጋጣሚ የታጋቾቹ ተማሪዎች ቤተሰቦች ብርታቱን እንዲሰጣችሁና ውዶቻችሁ በሰላም እንዲቀላቀሏችሁ አስተባባሪ ግብረሀይሉ ያለውን ልባዊ ፅኑ ምኞች ለመግለፅ ይወዳል። በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት ከጎናችሁ መሆኑንም ያረጋግጣል።

ፈጣሪ የታጋቾችን ነብስ ይታደገልን!!
ሀገራችንን የጎሳ ፖለቲካ ከሚያመጣው መአት ጠብቅልን!!

የጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ አስተባባሪ ግብረ ሀይል።