አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 3፣2012

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የታላቁ የህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ሲያካሂዱት የቆየው የቴክኒክ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚሰጠው ትርጉም፣ ግብፅ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ካልሆነም ግድቡ በተገቢ ዓመታት ውስጥ በውኃ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላት ነው ሲሉ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ሲካሄዱ በቆዩት የቴክኒክ ውይይቶች ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉንና በግብፅ ወገን ውሳኔ ለመስጠት የሚችለው አካል በዚህ ድርድር ውስጥ አለመኖሩን እንደሚያሳይ ኢትዮጵያ ማሳወቋ አይዘነጋም።

ሚኒስትሩ፣ ስምምነት ከሌለ ግብጾች ግድቡ በተገቢዎቹ ዓመታት ውስጥ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለዋል።

ግድቡ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ማን ነው ኦፕሬት የሚያደርገው የሚል ጥያቄ ከአንድ የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኛ ለሚኒስትሩ ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን፣ ሚኒስትሩም መገረምና ግራ መጋባት በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ ሆነው፣ ‹‹ይህ የእኔ ግድብ ነው! የእኔን ግድብ ማን ሊያስተዳድረው ይችላል?›› ሲሉ ለጥያቄ አቅራቢዋ ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥያቄ ያቀረበችው ጋዜጠኛም በግብፅ በኩል ግድቡን የማስተዳደር ፍላጎት ከዚህ ቀደም ሲንፀባረቅ የነበረ በመሆኑ ምናልባት በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት ተነስቶ እንደሆነ በማሰብ ያነሳችው መሆኑን በመጥቀስ፣ ለሚኒስትሩ ጥያቄ ያዘለ ምላሽ በድጋሚ ሰንዝራለች።

እንዲህ ዓይነት ሐሳብም ሆነ ጥያቄ በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት ከግብፅ ወገን አለመነሳቱን ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ የግድቡ ባለቤት ግድቡን እንደሚያስተዳድር ነገር ግን ይህንን በሚያደርግበት ወቅት ከታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር መረጃ በመለዋወጥ፣ በትብብርና ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚያስችሉ የመፍትሔ ሥልቶችን በመጠቀም እንደሚሆን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝ ላይ ለተፈረሙና አባል ላልሆነችባቸው የቅኝ ግዛትና ድኅረ ቅኝ ግዛት ኢፍትሐዊና አግላይ፣ ‹‹ውሎች›› ዕውቅና እንድትሰጥ የሚደረጉ ሙከራዎችን እንደማትቀበል አስታውቋል፡፡