አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 3፣2012

በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ በታጣቂዎች የታገቱ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ትናንት ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጅ፤ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገና እህቱ እንደታገተችበት የተናገረው አንድ ግለሰብ ግን አሁንም ድረስ እህቱም ሆነች ሌሎቹ ተማሪዎች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃው እንደሌለው ተናግሯል።

”እህቴ እስካሁን አልደወለችልኝም፤ ማንም የደወለልኝም ሰው የለም። ተማሪዎች ተለቅቀዋል የሚለውን ዜና ከሰማሁ በኋላም ሌሎች ልጆቻቸው የታገቱባቸው ቤተሰቦች ጋር በስልክ ተገናንኝተን ነበር፤ እነሱም እስካሁን ምንም መረጃ የላቸውም” ብሏል።

አክሎም ”እኔም ደወልኩላቸው፤ እነሱም ደወሉልኝ። ነገር ግን ማንኛችንም ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ከመንግሥትም ሆነ ከተማሪዎቹ ራሳቸው የተነገረን ነገር የለም” ብሏል።

ሌላኛዋ ወንድሟ ከታጋች ተማሪዎች መካካል አንዱ እንደሆነ የገለጸችው ወጣትም እስካሁን ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የሰማችው ነገር እንደሌለ ትናገራለች።

”ትናንት ዜናውን ከሰማንበት ሰዓት ጀምሮ በጉጉት እየተጠባበቅን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ወንድሜም አልደወለም፤ ሌላ የደወለልኝም አካል የለም” ብላለች።

ተማሪዎቹ ተለቀዋል የሚለው ዜና ከመሰማቱ በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸውን ለልጆቹ ደህንነት ሲባል ያልጠቀሱት የታገቱት ተማሪ ቤተሰቦች፤ ተማሪዎቹ ከታገቱ አንድ ወር እንዳለፋቸው ይናገራሉ።

“በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ስልክ ይደውሉ ነበር፤ አሁን ግን ድምፃቸውን ከሰማን ሦስት ሳምንታት አልፈዋል” ይላሉ።

ከአጋቾቹ እጅ ያመለጠችው አስምራ እንደምትናገረው፤ አጋቾቹ በተደጋጋሚ “ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም። ጸባችን ከመንግሥት ጋር ነው” እንደሚሉ ትናገራለች።

አጋቾቹ “የአማራ ሕዝብ ልጆቻችን ታግተዋል ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፤ መንግሥት እኛን ያነጋግራል። የዛኔ እኛ ጥያቄያችንን ለመንግሥት እናቀርባለን፤ ጥያቄያችንም ይመለሳል” እንዳሉ አስምራ ገልፃለች።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች የሉም ብለዋል።

ኃላፊው “ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም” ከማለት ውጪ ማብራሪያ መስጠት አልፈለጉም።