አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 3፣2012

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በተፈጠረ የዝናብ እጥረት በታኅሣሥ በተጠና ጥናት 103 ሺህ 32 ዜጎች ጊዜያዊ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚፈልጉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአካባቢው መሠል የድርቅ ክስተት ሲኖር አማራጭ የሥራ ዕድል ማዕከላት አለመኖር ዜጎች ስደትን አማራጭ እንዲያደርጉ አስገድዷል፡፡

መንግሥት ሁልጊዜ ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ዘላቂ የመፍትሔ ሐሳቦችን በዕቅድ እንዲፈታም ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

ድርቅ በተከሰተበት የፃግብጂ ወረዳ የሚኖሩትን አቶ ካሱ ወልደየስ  ‹‹ድርቁ ጊዜያዊ ችግር ነው፤ ጊዜያዊ ችግሮችን አሸንፎ ለመኖር ግን ሌላ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የተመለሱለት ሕዝብ ባለመሆኑ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል›› ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታን ያነጋገረው የአማራ  መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ‹‹እስከ ፌዴራል በተደረገ የድርቅ ተጋላጮች ዳሰሳ 103 ሺህ 32 ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜያዊ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ እንደሆነ ተረጋግጧል›› ብለዋል ሲል ዘግቧል።

65 ሺህ 217 እንስሳት ደግሞ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲሰደዱ በቅርብ ድጋፍ የሚፈልጉ በቁጥር ያልተረጋገጡ እንስሳት ደግሞ አስቸኳይ የምግብና የመጠጥ ውኃ ድጋፍ እንደሚሹ ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አስተዳድሩ ስሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ ሰቆጣና ፃግብጂ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 47 ቀበሌዎች በምግብ ራሳቸውን ለማይችሉት ብቻ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን የጋዝጊብላ እና ድሃና ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ቆላማ አካባቢዎችም በድጋፉ የሚሳተፉ እንደሆነ ተናግረዋል።

‹‹አስቸኳይ ድጋፉ በሚፈለገው ያክል አለመሠራጨቱ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እንዲበዛ አንድ ምክንያት ሁኗል›› ያሉት አቶ መልካሙ ወረዳዎች ለዚህ ዳካማ አፈፃፀም ተጠያቂ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ድጋፍ ለማድረግ የትራንስፖርት እጥረት፣ የሥራ ኃላፊዎች የመረጃ አያያዝ ችግር እና ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

የፃግብጂ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታወይ አብርሃ ‹‹የስደቱ መነሻ በዝናብ እጥረት የተፈጠረ ድርቅና የሥራ ዕድል አለመፍጠር ነው›› ብለዋል።

ወረዳው አዲስ በመሆኑ እና በአካባቢው ከመሠረተ ልማት ጀምሮ ኢንቨስትመንቶች ባለመኖራቸው ዜጎች ወደ ከተማ እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።