አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 3፣2012

‹‹የሁለቱ ሕዝቦች እሴት አልተሸረሸረም፤ ግጭቶች ሲፈጠሩ የዘር መልክ የሚያሲዙ የዘር ነጋዴዎች ሴራና ሥራ ነው›› ሲሉ የአማራ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተናግረዋል፡፡

የአፋርና የአማራ ክልል ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ በሠመራ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ የሁለቱ ሕዝቦች ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ሥነ መንግሥታዊ ግንኙነቶች ከጥንት እስከ ዘመናችን የዳሰሰ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ሁለቱ ሕዝቦች በተለይም በሀገራዊ አንድነት ላይ የነበራቸው እሳቤ ለትብብራቸውና ተመሣሥሏቸው ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝ ተመላክቷል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፉ በኋላ ተወያዮቹ መሠል የሕዝብ ለሕዝብ ግኙነቶች እስከታችኛው እንዲወርዱ፣ እየታዩ ያሉ ሃይማኖታዊ ግጭቶች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው፣ ለሀገራዊ አንድነት ትኩረት እንዲሰጥ፣ የሁለቱ ክልሎች ልማታዊ ግንኙነቶች እየተቀዛቀዙ መምጣት ትኩረት እንዲሰጠውና የመንግሥት የግጭት አፈታት ሥርዓት በሀገር በቀል እሴቶች እንዲታገዝ የሚሉ ጥያቄዎችና ምክረ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች መላሽ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በቀጣይ ዘርፈ ብዙ በሆኑ የልማት ሥራዎች ክልሎቹን በልማት ለማሥተሣሠር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የሐሰት ወሬዎች የግላቸውም ሆነ የመንግሥታቸው አቋም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የአማራ ክልልን መንግሥት ከሃይማኖት አንጻር ለመወንጀል የተደረገው ሙከራ መሠረተ ቢስ ነው›› ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ቧያለው ‹‹የክልሉ መንግሥት ቤተ እምነቶች ሲቃጠሉ መግለጫ አልሰጠም፤ ይህም ነገሮችን ረጋ ብለን ለማየት የተደረገ ነው›› ብለዋል፡፡

አማራ ክልል ላይ ሰልፎች ሲደረጉ ሀገር የፈረሰ የሚመስላቸው ብዙዎች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ ‹‹የሁለቱ ሕዝቦች እሴት አልተሸረሸረም፤ ግጭቶች ሲፈጠሩ የዘር መልክ የሚያሲዙ የዘር ነጋዴዎች ሴራና ሥራ ነው›› ሲሉም በሁለቱ ክልሎች ብሔርንም ሆነ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት አለመኖሩን ተናግረዋል ሲል የአብመድ ዘግቧል፡፡