አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 3፣2012

የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት የቅድመ ፓርቲ ምስረታ ለማድረግ ዛሬ በኢንተር ኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል የጠራውን ዝግጅት እንዳናደርግ መንግስት ክልከላ አድርጎብኛል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚጠይቀውን የቅድመ ፓርቲ ምስረታ ለማድረግ ሁለት መቶ ሰዎችን ለመመዝገብ የሚያሥችል የምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰነድ ወስደን ዛሬ እሁድ ጥር ሶስት ቀን 2012ዓ.ም ከጠዋቱ 3ሰዓት ላይ ቀድመን የአዳራሽ ኪራይ ከከፈልንበት ሆቴል ላይ ስብሰባችንን እንዳናደርግ ክልከላ ተደርጎብናል ሲሉ አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው የባለ አደራ ምክር ቤቱ የህግ ባለሙያ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ገልጸውልናል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሊያሟላ የሚገባውን ሁኔታ ሁሉ ለማሟላት የምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልተናል የሚሉት አቶ ሄኖክ አስፈጻሚው አካል ጫና እያደረገብን ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሄኖክ ገለጻ ባለ አደራ ምክር ቤቱ በፖለቲካ ፓርቲነት ተመዝግቦ ለምርጫ ከቀረበ አዲስ አበባ ላይ የማሸነፍ አቅም ያለው በመሆኑ መንግስት የፓርቲነት እንቅስቃሴውን የማደናቀፍ ስራ እየሰራብን ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሚል ስያሜ እንዳገኘ የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ገልጸው ነገ ሰኞ ሶስት ሰዓት ወደ ምርጫ ቦርድ በመሄድ ተገቢውን የፖለቲካ ፓርቲነት ቅድመ ሁኔታ እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡

ዛሬ የተደረገብን ክልከላ እኛን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሁሉ እንደሆነ ነው የምናስበው የሚሉት አቶ እስክንድር ክልከላ ከተደረገ የምርጫ ቦርድ ህግ እየተጣሰ እንደሆነ ነው የምናስበው ብለዋል፡፡