አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 4፣2012

በቅርቡ በአዲስ አበባ በይፋና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እየተጀመሩ ያሉ ፕሮጀክቶችና የመሬት ዕደላ በመስተዳድሩ ውስጥ ከፍ ያለ ግራ መጋባትና ድንግርግር ማስከተላቸውን ከከተማው አስተዳደር የተለያዩ ሀላፊዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በለገሀር የንግድ መርከብ ህንጻና ታሪካዊው ቡፌ ዴላጋር ፈርሶለት ፤ ሌሎች በርካታ የመኖርያ ቤቶችም ይነሱለታል ተብሎ የሚጠበቀውና ብዙ የተባለለት የአቡዳቢው ኤግል ሂልስ ኩባንያ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን የሽያጭ ማስታወቂያን ስለኩባንያው ከዚህ ቀደም በሌሎች ሀገራት የተፈጠረው ውንብድና ወደ እኛ ሀገር ስላለመምጣቱ መተማመኛ የሚሰጥ አይደለም ሲሉ የመስተዳድሩ ሀላፊዎች ስጋታቸውን ይናገራሉ።

ይህ ኩባንያ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነው።

በሌሎች ሀገራት በሰራቸው ስራዎች ቅሬታ ሲሰማበት የቆየው ኤግል ሂልስ በለገሀር 36 ሄክታር መሬት እንደሚቀርብለትና ፣ የኢትዮጵያ መንግስት 20 በመቶ አካባቢ ድርሻውን በሚያዋጣበት በጥቅሉ በ50 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎችን እና ቅንጡ መኖርያ ቤቶችን እንደሚሰራ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

ኤግል ሂልስ በለገሀር ላይ ሊሰራ ላሰበው ፕሮጀክት ያቀረበው ዲዛይንም ቢሆን የከተማዋን ማስተር ፕላንና ታሪካዊ ቅርሶችን አደጋ ውስጥ የጣለ ነው በሚል ማስተካከያ እንዲያደርግ ተመክሮ ነበር።

አሁንም ቢሆን በቀረቡለት ምክረ ሀሳቦች መሰረት እየሰራ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምሩ የቡፌ ደላጋር መፍረስን ጨምሮ ሌሎች ፍንጮች አሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዘጋጃ ቤት እድሳትም ሌላው በጨረታ ያልተሰጠ ፕሮጀክትና ከወዲሁም ችግሮች ይታዩበት የነበረ እንደሆነም ሰምተናል።

በ30 ሺህ 300 ካሬ ላይ የአድዋ ፓርክን እንዲሰራ የ4.6 ቢሊየን ብር ውል የወሰደው የቻይናው ጂያንግሱም ያለ ጨረታና ያለ ግልጽነት ያገኘው ውል ነው።

የአዲስ አበባ የወንዞች ልማትም ፕሮጀክትም ተመሳሳይ ትችቶች ያሉበት ነው።

ጎተራ በተለያየ ባለቤቶች ይሰራሉ የተባሉ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችም የፕሮጀክቶቹ ግንባታ አሰጣጥ ከግልጽነት የራቀ ነው ተብሏል።