አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 4፣2012

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ 50 ቢሊዮን ብር የባንክ እዳ እንዳለበት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

የከተማው ካቢኔ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የመንግስት ተጠሪዎች የአስተዳደሩን የለውጥ ስራዎች አብራርቷል።

የቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላትም አጽንዖት እንዲሰጠው ከጠየቋቸው ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤት ግንባታ መዘግየት፣ የመሬት ወረራና የሰነድ አልባ ይዞታዎች ዋነኞቹ ናቸው።

ግንባታቸው ከተጠናቀቁ 51 ሺህ ቤቶች ውስጥም 9 ሺህ ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል ጋር የወሰን ጥያቄ ስለተነሳባቸው አለመተላለፋቸውን ገልጸው ሌሎች ግን ሙሉ በሙሉ መተላለፋቸውን ተናግረዋል።

በመሃል ከተማዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 38 ሺህ ቤቶችም ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ ምክትል ከንቲባው ጨምረው ገልጸዋል።

ኢንጂነር ታከለ የቤት ባለዕድለኞች ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ማቃለል እንደተቻለ ጠቁመው አሁንም ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት ቤቶች ማስተላለፍን በተመለከተ በርከት ያሉ ባለድርሻዎች ይሳተፉ እንደነበርና አሁን ግን ከተማ አስተዳደሩና ዕድለኞች ብቻ እንደሚሳተፉበትም ተናግረው፤ ቤቶች በፍጥነት ተገንብተው ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው የከተማ አስተዳደሩ 50 ቢሊዮን ብር የባንክ እዳ እንዳለበት ገልጸዋል።

እነዚህ ቤቶች 40-60 እና 20-80 የቤት ልማት መርሃ ግብር የተገነቡ መሆናቸውንና ይህ የሆነው ቤቱን የወሰዱ ሰዎች በትክክል ወለድና ኢንሹራንስ መክፈል ባለመጀመራቸው ነው ይላሉ።

በተጨማሪም 130 ሺህ ቤቶች ተገንብተው በወቅቱ ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው እንዲሁም በአጋጣሚ የተላለፉትንም ግለሰቦች ገብተው ኑሮ ባለመጀመራቸው እንደሆነም አብራርተዋል።

”ይህ መሆኑ ደግሞ የመንግስት ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ በመሆኑ ከባንክ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን” ብለዋል።

ዘንድሮ በከተማው 50 ሺህ ቤቶች ለመገንባት የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 17 ሺህ ቤቶች በመንግስት ቀሪዎቹ ደግሞ በግል የሚገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።