አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 4፣2012

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት ባለፈው ባካሄደው ጉባኤ ማጠናቀቂያ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ሲያወጣ ካነሳቸው አንኳር ነጥቦች አንዱ በቀጣይ ከኤርትራ ጋር ስለሚኖረው የመልካም ግንኙነት ፍላጎት አዝማሚያ ኤርትራዊያን ምሁራንን አስቆጥቷል፡፡

ሙሴ ስብሀቱና እና የዕብዮ ዩሃንስ የተባሉ ኤራትራዊያን ፖለቲከኞች ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ ህወሃት ያቀረበውን የትግራይና የኤርትራ ወዳጅነት ማጠናከሪያ ሀሳብ ውድቅ አድርገዋል፡፡

ፖለቲከኛው የዕብዮ ስብሃት ህወሃት ባለፉት ጊዜያት ስትከተለው ከነበረችው የግደለውና አጥፋው እንዲሁም ጨፍጭፈው ከሚል ሀሳብ ወጥተው ስለኤርትራ ሰላምና ሉዓላዊነት ማውሳታቸው መልካም ቢመስልም ህወሃት እንደ ድርጅት ቤት ዘግታ ስትፎክርና ስትሸልል ኖራ በመግለጫዋ ብቻ ስለ ኤርትራ ወንድማዊነት ማውረቷ ከንቱ አንደሆነ መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡

ፖለቲከኛው ሚስትህን የሚመኝ ጓደኛህ ሊሆን አይችልም በማለት በጠቀሱት ብሂል ከመቶ ሺህ በላይ ህዝብ ካለቀበትና በርካታ ወጣቶች በስደት ከጠፉበት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት የተፈጸመውን የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ሳይደረግ ስለሰላም ማውራት አሳማኝ አይደለም ያሉ ሲሆን የባድመ መሬት ለኤርትራ አንዳይሰጥ ያደረገችው ህወሃት ስለእርቅና ወዳጅነት ማውራቷ ዋጋ ቢስ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተመመሳሳይ ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ሌላኛው ኤርታራዊ ፖለቲከኛ ሙሴ ስብሃቱ ህወሃት የትግራይና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማቾች መሆናቸውን ለመግለጽ መሞከሯ ትክክል ቢመስልም ከትግርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ከ8 በላይ ማንነት ባላት ኤርትራ ሰለ አንድ ማንነትና ቋንቋ ብቻ ማውራት ድብቅ የሆነ ኤርትራዊያንን የማለያየት ሴራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ፖለቲከኛው አክለውም እርቁ መሬት አልወረደም በዶ/ር አቢይና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መካከል ነው ስምምነት የተፈጠረው የሚባለው ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን ከኢትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም በኋላ በበርካታ አጋጣሚዎች ህዝቡ በየብስም ሆነ በአየር ትራንስፖርት እየተገናኘ ናፍቆቱን እየተወጣ እንደሆነ መካድ የለብንም በማለት አብራርተዋል፡፡

የህዝብ ለህዝብ መቀራረብም በመንግስታት ወዳጅነት እንደሚወሰን መገነዝብ ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡