አባይ ሚዲያ ዜና-ጥር 5፣2012

አዲስ አበባ የሚገኘው የትግራይ ቴሌቪዥን የአማርኛው ክፍል ባልደረቦች ለስራ በሔዱበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ መታሰራቸውን ትግራይ ቴሌቪዥን የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናገረ።

የዝግጅት ክፍሉ ተወካይ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አለማየሁ እንደተናገሩት በአሶሳ ከተማ በሚካሄደው እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው የዜና ሽፋን እንዲሰጡ ወደ ዝግጅት ክፍሉ በተላከው ግብዣ መሰረት ወደ ስፍራው “የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኛ የሆነው ዳዊት ከበደ እና የካሜራ ባለሙያው በሀይሉ ውቤ መላካቸውን አስታውቀዋል፡፡

አዲስ አበባ ከሚገኘው የጣቢያው ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ አሶሳ ያመሩት ባልደረቦችም ከቅዳሜ ጀምሮ የተለያዩ ቀረፃዎችን ሲያካሂዱ ቆይተው ትናንት ጥር 4/2012 ዓ.ም ምሽት ላይ እራት ተመግበው ወደ ማደሪያቸው ሲመለሱ ሶስት ሰአት ገደማ ላይ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዜናውን አጠናቀው ሰርተው ዛሬ ጥር 5 ወደ መስሪያ ቤታቸው ተመልሰው ሪፖርት ማድረግ ቢኖርባቸውም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዝግጅት ክፍሉ ገልጧል፡፡

የትግራይ ቲቪ የአዲስ አበባ ቢሮ አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ደባልቀው እንዳሉት ከሆነ እዛ ሆነው የሰሩት እና በቲቪ የተላለፈ ፕሮግራም እንኳን አልነበረም።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ መለሰ በየነ በጉዳዩ ዙሪ በሰጡት ማብራሪያ”እኔ ለስራ ሌላ ቦታ ነኝ ነገር ግን ስልክ በመደወል ለመረዳት እንደቻልኩት ጋዜጠኞቹ የነበረንን አሰራር ተከትለው አልመጡም።

ይህ ማለት ደግሞ ወደ ክልሉ ለዘገባ እንደሚመጡ ለክልሉ ኮሚኒኬሽን አላሳወቁም።

ሃላፊው አክለውም ምን መስራት እንደሚፈልጉ ነግረውን፣ እኛም ባለሙያ እና አስፈላጊም ከሆነ የፀጥታ አካላት መድበን መሆን ነበረበት ያሉ ሲሆን ለምሳሌ እኔ እንደ ክልሉ ኮሚኒኬሽን ሀላፊ ስለመምጣታቸው የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

ታሰሩ ሲባል እንደሌላው ሰው ነው የሰማሁት ያሉት ኃላፊው አሁን ግን የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ በትክክል አጣርተን እናሳውቃለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።