አባይ ሚዲያ ዜና-ጥር 5፣2012

በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በተነሳው ግጭት ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ከደምቢ ዶሎ ወደ ጋምቤላ ሲያቀኑ ሱድ የምትባል ቦታ ላይ እገታ የደረሰባቸው ተማሪዎች አሁንም እንዳልተለቀቁ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በድርድር ለማስለቀቅ ችለናል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በበኩላቸው ተማሪዎች ተለቀው በመንግስት እጅ ስር ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ነገር ግን ዛሬም የተማሪ ወላጆች ከታጋች ልጆቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

የተማሪ ቤተሰቦች ዩኒቨርሲቲው ድረስ ሂደው ማጣራት ለማድረግ የሚያደርጉት ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸው መንግስት ታጋቾቹን ማስለቀቅ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

ከአጋቾች ያመለጠችው ተማሪ አስምራ ሹሜ ከታጋቾች ጋር ባደረገችው አጭር የጽሁፍ መልዕክት በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር እንደሚያደርጉባቸው የነገሯት ሲሆን ወንዶችን ደግሞ መደብደብና ለስቃይ እንደዳረጓቸው ገልጸውልኛል ስትል ገልጻለች፡፡