አባይ ሚዲያ ዜና-ጥር 5፣2012

የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ በተካረረበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ሀገራቱን ለማስማማት አዲስ የስምምነት ስነድ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላት ተገልጧል።
የዓለም ባንክና ዩናይትድ ስቴትስ ላለፉት ሁለት ወራት በታዛቢነት ሲከታተሉት የነበረው የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ሊፈታ ባለመቻሉ የየሀገራቱ ባለስልጣናት ዋሽንግተን ላይ ለውይይት ታድመዋል።
የዋሽንግተኑ ስብሰባ ዓላማ እስካሁን የተደረጉ አራት ስብሰባዎችን ውጤት ለመነጋገር ቢሆንም በአሜሪካ በኩል ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን የሚፈቱበትን መንገድ ያካተተ አዲስ የስምምነት ሰነድ ሀገራቱ እንዲፈርሙና ድርድሩ እንዲቀጥል የሚል ፍላጎት አላት።

የድርድሩን ጊዜ ማራዘም የሚል ሀሳብም አማራጭ አንደሆነ ተሰምቷል።

በአሜሪካ ጠሪነት በተጀመረው ይህ ስብሰባ ተጨማሪ ሁለት የዋሽንግተን ስብሰባዎችም ይደረጉበታል የሚል ስምምነት የነበረው ነው።

አለም ባንክና አሜሪካም የውይይቱ ታዛቢ እንደሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። በዋሽንግተን የሚደረጉት ሁለት ስብሰባዎች የቴክኒክ ሳይሆኑ በሶስቱ ሀገራት የሚደረጉ ውይይቶች ሪፖርት ይቀርብበታል የተባለ ሲሆን ስብሰባው በትላንትናው እለት ተጀምሯል፡፡

ይህ ስብሰባ አራቱ ቴክኒካዊ ስብሰባዎች ከምን እንደደረሱ ለመነጋገር እንጂ ቴክኒካዊ እንዳልሆነም ተገልጧል።

አሜሪካ ግን በዚህኛው የዋሽንግተን የህዳሴው ግድብ ስብሰባ ላይ ስምምነት የማፈራረም ፍላጎት እንዳላት ተሰምቷል፡፡

ሶስቱ አገራት በዋሽንግተን ዲሲ በደረሱት ስምምነት አማካኝነት ስምምነት ላይ ካልደረሱ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በካርቱም የተፈረመው ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል።

የካርቱም ስምምነት አንቀጽ 10 “ሶስቱ አገራት በመርሆዎች ስምምነቱ አተረጓጎምና ተግባራዊነት የተነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ለአገራቸው መሪዎች ሊያሳውቁ ይችላሉ” ይላል።

ግብጽ አራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ተጠናቀው አሜሪካና አለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራት ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪ እንዲሆን ፍላጎት አለ።

አሜሪካና የአለም ባንክ በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ወቅት ለስሙ ታዛቢ ብቻ ናቸው ቢባልም በካርቱምና በአዲስ አበባ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሙሉ ለሙሉ አደራዳሪ ሆነው ሲሰሩ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል ስትል ዋዜማ ዘግባለች።