አባይ ሚዲያ ዜና-ጥር 5፣2012

የቤኒሻንጉል ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ›› የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ የነበሩ 10 ግለሰቦች ላይ የእስር ማዘዣ በማውጣት ሰብሳቢውን ጨምሮ አራት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

የፓርቲዉ ምክትል ሰብሳቢ ጌታሁን መርጋ፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጌታቸዉ ወድሻ፣ የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ጉዮ ፈረደን  ሐሙስ ታኅሳስ 30/2012 መታሰራቸውን የቦሮ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዮሐንስ ተሰማ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጥር 01/2012 በፓርቲው የቡለን ወረዳ የወጣቶች ኃላፊ የሆኑት ታምራት ጎዶሶ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

የፓርቲዉ አመራሮች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአሶሳ ዩንቨርሲቲ ችግር እንዲፈጠር አድርጋችኋል በሚል የነበር ቢሆንም፣ ጥር 01/2012 ሐሳቡ ተቀይሮ ‹‹የክልሉ ምክር ቤት የፋይናንስና ገንዘብ ቋሚ ሰብሳቢ በሆኑት በአብደላሂ ሀጂ ግድያ እጃችሁ አለበት›› ተብሎ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ፓርቲዉ በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ በሚደርገዉ ሂደት በምርጫ አዋጁ መሰረት መስፈርቱን አሟልቶ እውቅና ለማግኘት በአሶሳ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት በተሰባሰቡበት ወቅት፣ በክልሉ ፖሊስ እንደታገዱ ዮሐንስ አስረድተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ፓርቲዉ የሚያደርገውን ትግል ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ጫና እያሳደረበት ነው ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

‹‹በአሁኑ ጊዜም ቀሪ የፓርቲዉ አመራሮችን እኔን ጨምሮ ለማሰር የክልሉ ፖሊስ እየፈለገን ነው›› በማለት ከክልሉ ተሸሽገው እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ቦሮ ፓርቲ የሽናሻን ሕዝብ ወክሎ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በምርጫ ቦርድ እውቅና ለማግኘት አስፈላጊዉን ሁሉ አሟልቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን የሚገልፁት ዮሐንስ፣ ‹‹ክልሉ ይህንን እንቅስቃሴያችንን አስተጓጉሎታል›› ብለዋል።

ጉዳዩን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸዉን ተከትሎ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን እንዲያቆም ደብዳቤ መጻፋቸዉን በስልክ እንደነገሯቸዉ አዲስ ማለዳ ዘግቧል።