አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 6፣2012

በበርካቶች ሀገር በተለይም ኦሮሚያን እያመሰ ነው የሚል ወቀሳ የሚቀርብበት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የቀድሞ የኦነግ ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ በትግል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ጃል መሮ በምዕራብ ኦሮሚያ እየተከናወነ ስላለው ጉዳይ ለቢቢሲ አቋሙን አሳውቋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች ዜናን መስማት የተለመደ ሆኗል።

የጥቃት ዒላማዎቹ የሚያነጣጥሩት በአካባቢው ባለሥልጣናት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ለሥራ ወደ ወለጋ ዞኖች የሚንቀሳቀሱ ኃላፊዎችንም የሚጨምር ሲሆን ለእነዚህም ባለሥልጣናት ግድያ ተጠያቂ የሚደረገው በጃል መሮ የሚመራው የታጣቂ ቡድን ነው።

ነገር ግን መንግሥት የእርሱን ጦር ለማዳከም እየተጠቀመበት ያለው ስትራቴጂ መሆኑን እንጂ የእርሱ ጦር ይህን መሰል ተግባር እንደማይፈጽም የሚናገረው ጃል መሮ “በምስራቅ በኩል ኦሮሞን እና ሱማሌን እንዳጫረሱት ሁሉ አሁንም በዚህ በኩል የኦሮሞ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለማጋጨት ነው” ይላል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንደሚገኝ ቢታወቅም የአገልግሎቶች መቋረጥን አስመልክቶ ከኢትዮ ቴሌኮምም ይሁን ከመንግሥት የተሰጠ በቂ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

የቴሌኮም አገልግሎቶቹ እንዲቋረጡ የተደረጉት መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ላይ ኦፕሬሽን እያካሄደ ነው የሚሉ መላ ምቶች በስፋት ሲነገሩ ቆይቷል።

የስልክና የሞባይል ዳታ ግንኙነት መቋረጡን የሚናገረው ጃል መሮ፤ “እንዳሰቡት በኦሮሞ ነጻነት ጦር ሊገኝ የታሰበው የበላይነት መሳካት ስላልቻለ በተለየ መንገድ ሊሄዱበት የወሰኑት ውሳኔ ነው እየተካሄደ ያለው” ይላል።

“መንግሥት ሲፈልግ አገልግሎቱን ለአንድ ዓመት ይዝጋው። ጦራችን በየዕለቱ በተሟላ መልኩ ግንኙነት ማድረጉን እንደቀጠለ ነው።

ኪሳራው ለመንግሥት እንጂ በእኛ ግንኙነት ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም” በማለት የተሟላ አገልግሎት እንዳለው ጠቁሟል።

ጃል መሮ ከሌሎች አካላት ጋር አብሮ እየሰራ ነው ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ሲሰጥ፤ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ከሚደግፉ ማናቸውም አካላት ጋር አብረን ልንሰራ እንችላለን፤ ይሁን እንጂ እንደሚባለው ከህወሃት ጋር አብረን ልንሰራ አንችልም። ብዙ ጠባሳ አለብን ከህወሃት ጋር ፈጽሞ ልንሰራ አንችልም” ብሏል።