አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 6፣2012

ምርጫ ቦርድ ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም እንደሚካሄድ ዛሬ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የምርጫ መርሃ ግብር ውይይት መድረክ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡

የወጣውን ፕሮግራም ተከትሎም የተለያዩ ሀሳቦች የተሰጡ ሲሆን ከፖለቲካ ፓርዎችም በተወሰነው ቀን ላይ የድጋፍና የነቀፌታ አስታየቶች ተሰንዝረዋል፡፡

የኢትዮጲያዊያን ሃገራዊ ንቅናቄ /ኢሃን / በሃገራችን አሁን ላይ ባለችበት ሁኔታ ምርጫ ነሃሴ ወር ላይ የሚካሄድበት አግባብ የለም ይላል፡፡

የፓርቲው ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ትምህርት ቤቶችና ፓርላማው በሚዘጉበት በክረምት ወቅት ምርጫን አካሂዳለሁ ማለት ቀልድ ነው ሲሉ ተናግረው ይህ የህዝብን ድምጽ ለመስረቅ እንዲመች የተደረገ ስራ ይመስላልም ብለዋል ኢንጅነር ይልቃል።

በመሆኑም ፕሮግራሙ በፓርቲያቸው ተቀባይነት የሌለው ፕሮግራም መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ደግሞ ምርጫው በየትኛውም ሰዓት ቢደረግ ለመወዳደር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የትኛውም ፓርቲ የሚዘጋጀውን ያክል ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ይሁንና የምርጫ ቦርድ መዋቅር እስከ ታች ድረስ መስተካከልና ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡

ቦርዱ ላይ ጥርጣሬ አላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ የታችኛው እርከን ላይ ለውጥ አለመኖሩንና ይህም ጥርጣሬ ውስጥ እንዳስገባቸው ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር ከተስተካከለ ነገም ቢሆን ለመወዳደር ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓም የሚካሄድ ሲሆን፤ የእጩዎች ምዝገባ ደግሞ ከሚያዚያ 13 ቀን እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓም ይከናወናል ብሏል።

የምረጡኝ ቅስቀሳ ደግሞ ከሚያዚያ 22 እስከ ነሀሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ይከናወናል።

በሂደቱም ላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተያየትና ግብአት ይሰጡበታል ተብሎም ይጠበቃል።