አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 7፣2012 ዓ.ም

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት የተከዜ ወንዝን ተሻግሮ እራሱን በወልቃይት ምድር ያገኜው ለመጀመርያ ግዜ በ1972 ዓ/ም ነበር። ከዚህ ግዜ ወዲህም ለተከታታይ 11 ዓመታት እስከ 1983 ዓ/ም መጨረሻዎቹ አካባቢ ቦታው የጦር ቀጠና አድርጎት እንደቆየና በኋላም በ1984 ዓ/ም ያለምንም የህዝብ ፍላጎት ህወሓት ኢህአዴግ ወልቃይትን ወደ ትግራይ ቀምቶ መውሰዱን ይታወሳል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ህጉን ተከትሎ ለፌደሬሽን ምክርቤት ቢያቀርብም ውጤቱ ግን የእስርና እንግልት ውርጂብኝ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው።

ወልቃይት የሚለውን ስም ሲጠራ የሚያንገበግባቸው ህወሓቶች ዛሬም ወልቃይትን ወደ 4 ቦታዎች በመከፋፈል ላይ እንዳሉ የዓባይ ሚድያ ምንጮች ይናገራሉ። በቅርቡ በነበረው የትግራይ ክልል ጉባኤ ወልቃይትን ወደ 4 ቦታዎች በማሳነስ/በመቆራረጥ የማይ ጋባ ከተማ አስተዳደር፣የቆራሪት ከተማ አስተዳደር፣አውራ ወረዳና እራሱ ወልቃይት ወረዳን በማለት ለ4 ከቆማመጡት በኋላ ለጥር 14/2012 ዓ/ም ቀርቦ እንደሚጸድቅና ከጥር 17/2012 ጀምሮ ደግሞ ተግባራዊ እንደሚሆን ለወረዳው ምክርቤት መናገራቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ይህንንም ያደረጉበት ምክንያትም ለምና ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከአካባቢው ተወላጆች ቀምተው በ1990ዎቹ ለሰፈሩት የትግራይ ተወላጆች ከመስጠት በተጨማሪ አዳዲስ ሰፈራዎች በማስመጣትና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ትግራይ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ከምንጮጫችን ሰምተናል። የወልቃይት ጠገዴ መሬት ማሽላ፣ጤፍ፣ዳጉሳ፣ሰሊጥና ጥጥ በዋናናነት ከሚያመርታቸው ምርቶች ሲሆኑ፣ኢትዮጵያ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች የሁመራው ሰሊጥ ቀዳሚው ተርታ ከያዙት ውስጥ መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።

የወልቃይት ህዝብ ለውጡን እንዲመጣ የመጀመርያ የትግል አቀጣጣይና ህጋዊነት የለለው መንግሥትን በድፍረት በጠብመንጃም ሳይቀር መታገል እንደሚቻል በተግባር ያሳየና ያረጋገጠ ቢሆንም ነገር ግን የለውጡ ተጠቃሚ አለመሆኑንና አሁንም መሬቱንና ሃፍት ንብረቱን በህወሓቶች እየተዘረፈ መሆኑን ይህ የአሁኑ የመሬት ክፍፍልና ዘረፋን አንድ ማሳያ ነው ሲሉም የዓባይ ሚድያ ምንጮች አክለዋል። ምንጮቹ የፌደራሉ መንግሥት አሁንም ልጆቻችን በሚለብሱት ማልያና በሚያዳምጡት ሙዚቃ ያለመመታት መብታቸውንም ጨምሮ አካባቢያችን ከሚከፋፍሉት ሃይሎች ሊታደገን ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።