አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 8፣ 2012

አቶ ለማ መገርሳ ከዚህ ቀደም ከብልጽግና ፓርቲ አመሠራረት ጋር ተያይዞ የነበራቸውን ልዩነት በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ በኩል በተደረገው ውይይት ተፈቷል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የከተሞች ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሳዳት ናሻ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ፤ በኢሕአዴግ ውህደት እና በጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር ፍልስፍና እንደማያምኑ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል።

ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የነበሯቸው ልዩነት በምን መልኩ ፈቱት? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም፤ አቶ ሳዳት ግን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባደረገው ውይይት ልዩነቶችን ቀርፏል ብለዋል።

አቶ ሳዳት መከላከያ ሚንስትሩ በሥራ ላይ ነው የሚገኙት ያሉ ሲሆን፤ ልዩነት ተፈጥሮ የነበረው ካለመግባባት እንጂ መሠረታዊ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ኖሮ አይደለም ብለዋል።

አቶ ለማ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በጉዳዩ ላይ የአቋም ለውጦች ሲኖራቸው ለመገናኛ ብዙኃን ወጥተው እንደሚናገሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፤ ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት በውይይት መፍትሄ አግኝቷል ሲባል፤ አቶ ለማ ወደ ሚዲያ ወጥተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብለው የጠበቁ በርካቶች ነበሩ።

አቶ ሳዳት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አቶ ለማ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይናገሩ ክልከላ ተደርጎባቸዋል የሚባለው ከጥርጣሬ የመነጨ ነው ይላሉ።

“ልዩነቱ በውይይት ተፈትቷል። ይሄ እውነት ነው። ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ በመግባባት እየተሰራ ይገኛል። አሁንም በኃላፊነት ላይ ነው ያሉት” ይላሉ አቶ ሳዳት።

“አቶ ለማ ካልተናገሩ በቀር የፓርቲው መግለጫ ስህተት ነው ብሎ ማሰቡ ትክክል አይደለም። በፓርቲው የተሰጠው መግለጫ፤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እና የጓድ ለማ አቋም ሆኖ መታየት አለበት” ብለዋል አቶ ሳዳት።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ከመካከለኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ባሉ ባለሥልጣናት ላይ ሹም ሽር እየተካሄደ ይገኛል።

ቀላል የማይባሉ የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰቦች ከሥራ እንዲነሱ እየተደረጉ ያሉት፤ የአቶ ለማ ሃሳብ ደጋፊዎች ናቸው የሚሉ መላምቶችን የሚሰነዝሩም አልጠፉም።

አቶ ሳዳት ግን፤ “ፓርቲው በራሱ ምዛኔ ባለሥልጣናትን ከቦታ ቦታ ያሸጋሽጋል። ምደባም ይሰጣል። እንዲህ አይነት ሹም ሽሮች የሚካሄዱት በአመለካከት ልዩነት ላይ ተመስረቶ አይደለም” በማለት “በአሁኑ ሰዓት ‘የፓርቲ አስተሳሰብ’ እንጂ ‘የአቶ ለማ ሃሳብ’ የሚባል ነገር የለም” በማለት የነበሩ ልዩነቶች መፈታታቸውን አስረግጠው ይናገራሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።