አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 9፣2012

እውቁ ፖለቲከኛ እና የኢዴፓ አመራር የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምራጫ ቦርድ የዘንድሮውን ሃገራዊ ምርጫ መርሃግብር ይፋ ሲደረግ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡

አቶ ልደቱ እንደሚሉት ምርጫ መካሄድ የለበትም ለሚለው ሀሳባቸው ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፕሬዝዳንት ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የተሰጠው ምላሽ ምክናያታዊ ያለሆነና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይሄን ታሪካዊ ሃላፊነት የተረከበው ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንድታካሂድ ነው የሚሉት አቶ ልደቱ ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበትና የፖለቲካው ዋና ተዋንያኖች ወደ ብሄራዊ መግባባት ባልመጡበት ሁኔታ እንዲሁም ፓርቲዎች እየወጡ ባሉ የምርጫ ህጎች ሳይስማሙ ምርጫ እናካሂድ ማለት ከአሁን በፊት በተደረጉ ምርጫዎች እንደማይሻል መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማድረግ ህግን እንደ ምክናያት ማቅረቡ ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጹት አቶ ልደቱ ምርጫው ወደ ከፍተኛ ችግር የሚወስደን ከሆነ ህግን ለማክበር ብለን ችግር ውስጥ መግባት የለብንም ብለዋል፡፡

አቶ ልደቱ ህግን ሰበብ እያደረጉ ወደ ግጭት የሚያስገባ ምርጫ እንዲካሄድ መከራከር አያስኬድም ሲሉም ምርጫ ቦርድ ወቅሰዋል፡፡

ፖለቲከኛው ህግ ለህዝብ የማይጠቅምና ሀገሪቷን ችግር ውስጥ የሚያስገባ ከሆነ የማይሻሻልበት ምክናያት የለም ሲሉ ጠቅሰው ከማንኛውም የመንግስት አካልም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ሀገሪቱ አሁን ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሰላም አላት በማለት በድፍረት የተናገረ የለም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ልደቱ ራሳቸውን የፌደራሊስት ሀይል ነን የሚሉ አካላትን እኛ ሀገር የሚበትኑ ሀይሎች ነው የምንላቸው፤ ምርጫ ቢካሄድ እንኳን እነሱን መምረጥ የ27 አመቱ ሀገርን የመከፋፈል ሂደት ይቀጥል ማለት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢዜማ አካሄድ ከእኛ ጋር የቀረበ ነው የሚሉት አቶ ልደቱ ነገር ግን የኢዜማና የብልጽግና ችግር የለውጥ ሂደቱና አተገባበሩ ችግር አልገለጸውም፤ ሀገሪቱ የህልውና ስጋት የለባትም ማለታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡