አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 9፣2012

በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በነበረው አለመረጋጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ የታገቱት ተማሪዎች ጥር 2ቀን 2012አ.ም መንግስት በድርድር ማስለቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሌታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ሌሎች 6 ተማሪዎች እንደሚቀሩና የማስለቀቁ ስራ እንደሚቀጥል ገልጸው ነበር ፡፡

ከእገታው የተለቀቁት ተማሪዎች የት ናቸው በሚል በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ደግሞ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ መንግስት ያስለቀቃቸው ሃያ አንድ ተማሪዎች ወደ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ሂደቱን የፌደራል መንግስቱ እንደሚከታተለው እና ከዩኒቨርስቲዎች፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደአካባቢው መላኩን ገልጸዋል፡፡

ታግተው የነበሩት ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርስቲው መመለሳቸውን የገለጹት ሃላፊው ተማሪዎቹ ከእገታ ከተለቀቁ በኋላ ከወላጆቻቸው ጋር ያልተገናኙት በአካባቢው የስልክ ግንኙነት አገልግሎት ባለመኖሩ የተነሳ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩን እንዲያጣራ ወደ ስፍራው የተላከው ቡድን ተማሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ገልጸዋል፡፡
የታገቱ ቀሪ ስድስት ተማሪዎችን ለማስለቀቅም ሌሎቹን ለማስለቀቅ የተደረገው ጥረት ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ሲሆን ይህ ካልተሳካ ግን ወደ አካባቢው ያቀናው ቡድን ያለበትን ደረጃ አጣርቶ ሪፖርት ያቀርባል ብለዋል፡፡

አጋቾቹን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦች የሚቀርቡ ሲሆን የክልሉ መንግስት አጋቹ እከሌ ነው የሚለው ነገር በግልጽ አለመኖሩን ገልጸው የአጋቹ ማንነት ተጣርቶ የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርስቲው የገቡት በመንግስት ጫና ነው ወይስ በፍላጎታቸው ተብለው የተጠየቁት ሃላፊው ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርስቲው የተመለሱት በፍላጎታቸው ይሁን በመንግስት ጫና መረጃው እንደሌላቸው ገልጸው ሆኖም ግን ተማሪዎቹ ተገደው ወደ ጊቢው ይመለሳሉ ብለው እንደማይገምቱ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፌደራል ፖሊስ እና የኢፌድሪ መከላከያ ሃይል መንግስት ከእገታው ስላስለቀቃቸው ተማሪዎች ምንም አይነት መረጃ የለንም ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡