አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 9፣2012

በውጭ ሀገራት ኑሯቸውን ያደረጉ የትግራይ ተወላጆች ማህበር ህወሃት እየሄደበት ስላለው አሳሳቢ መንገድ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁጣ አዘል መግለጫ አውጥቷል፡፡

ማህበሩ ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አገራዊ ጥቅም አሳልፈው በሰጡ ከሃዲዎችና ጸረ-ዲሞክራሲ በሆኑ ግለሰቦች የተመራ አሁንም የሚመራ ድርጅት  ስለሆነ፤ የድርጅቱ አቋሞችና ፖሊሲዎች የነዚህ በትግራይ እና በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብዙ ወንጀልና ዝርፊያ የፈጸሙ ግለሰቦች እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም ብሏል።

ህወሓት እንደ ድርጅት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለመዋሃድ መብት አለው ያለው ማህበሩ ችግሩ የአመራሩ መሰረታዊ ምክንያት “እኔ የማልመራው ውህደት መመስረት የለበትም“ የሚል ፍጹም ጸረ ዴሞክራሲ የሆነ ኣቋም ነው ሲል መወገዝ ያለበት የህወሓት አመራር የብልጽግና ፓርቲ መመስረት ለትግራይ ህዝብ አደጋ ነው ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔና በጉባኤውም የታየው የጦርነት ቅስቀሳ ነው ሲል አትቷል።

ማህበሩ በህወሓት ጉባኤ የተነሱትን ዋና ዋና የአቋም መግለጫዎችና በትግራይ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ብቻ ጥዬን አስተላልፋለሁ ያለ ሲሆን ምርጫን በሚመለከት በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ምርጫ ማካሄድ ቢቻል እንኳ፣ በትግራይ ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት በፍጹም የለንም ሲልም አብራርቷል።

የሃብትና የንብረት ክፍፍል በሚመለከት የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደዘረፉ የማይታበል ሃቅ ነው ያው ማህበሩ የህወሓት አመራር ይገባኛል ብሎ የሚጠይቀውን ንበረት ለተዘረፈው የኢትዮጵያ ህዝብ መመለስ እንዳለበት ያምናል፡፡

ማህበሩ አክሎም ህወሓት በስልጣን እስካለ ድረስ ፣ የትግራይ ህዝብ መብቶች እንደማይከበሩና እንዲያውም ይህ አመራር ስልጣኑን ለማስጠበቅ የትግራይን ህዝብ ጦርነት ውስጥ ሊማግደው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን ሲል እስካሁን ድረስ የህወሓት አመራርን በመቃወም ወደ ትግሉ ያልተቀላቀላችሁ የትግራይ ሊሂቃን፣ የትግራይ ህዝብ በአንድነትና በእኩልነት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ትግል የበኩላችሁን አበርክቱ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡