አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 9፣2012

እ.አ.አ 2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒክ አፍሪካን በቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የማጣሪያ ውድድር ተካሂዷል።

ከማጣሪያ ውድድሩ በተጨማሪ በትውልድ ኤርትራዊ በዜግነት ስዊድናዊ የሆነው ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብርና ኢትዮጵያዊው ካሳሁን ኃይሉ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው ነበር፡፡

ቢኒያም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የቻለው ዳኛቸው ዘርጋ ከሚባል የፌስቡክ ጓደኛው ጋር በመጻጻፍ እንደሆነና ዳኛቸው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን በማነጋገር ዕድሉን እንዳመቻቸለት ገልጿል።

“እናትና አባቴ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቴን ተከትሎ ከኤርትራ ሊያዩኝ መምጣታቸውና ከቤተሰቤ ጋር መገናኘቴ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል” ብሏል ቦክሰኛ ቢኒያም።

ቢኒያም አክሎም “የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ድሮም ቢሆን አንድ ናቸው ምንም የተለየ ነገር የለም አለመግባባቶች ነበሩ አሁን ግን መልሰው መገናኘት ጀምረዋል” ብሏል፡፡