አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 12፣2012

በሃረር የጥምቀት በዓል ላይ ተስተውሎ የነበረው የጸጥታ ችግር በመፍጠርና በዓሉን በማወክ በሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረመዳን ኡመር ዛሬ እንደገለጹት ከጥር 10/2012 ጀምሮ አንዳንድ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት በዓሉን ለማወክ ያደረጉት ጥረት በፀጥታ አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለመቆጣጠር ተችሏል።

በተፈጠረው የፀጥታ ችግርም 15 የጸጥታ አካላትን ጨምሮ በ19 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት እንዳጋጠመና በንብረት ላይም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደደረሰ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

እስከ አሁን ድረስም በድርጊቱ የተሳተፉ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራትና አስፈላጊው መረጃ በማሰባሰብ ተጠርጣሪዎቹ ለህግ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት በሀረር ተፈጠረ በተባለው ሁከት የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን በተለይም ታቦት እንዳያልፍ መንገድ ተዘግቷል የሚለውና ታቦቱ ከህዝበ ክርስቲያኑ በተጨማሪ በፖሊስና በመከላከያ ታጅቦ በሰላም መግባቱን የሚያመለክት ነው፡፡

የሀረሪ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊው በበኩላቸው “ትናንት ጠዋት ታቦት የሚሸኙ ሰዎች መንገድ ተዘግቶባቸዋል ስለመባሉ ተጠይቀው ” ማንም መንገድ የተዘጋበት የለም፤ ማንም መንገድ የዘጋም የለም” ብለዋል።

“ታቦት እንዳያልፍ አልተከለከለም፤ መንገዱም ክፍት ነው። ይሄ ተግባር ውዥንብር ለመፍጠርና ሕዝቡን በእምነት ስም ለማነሳሳት የሚደረግ ጥረት ነው” ሲሉም ሃላፊው አብራርተዋል።

በተጨማሪም ኃላፊው ”የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ለማክበርና አካባቢውን ለማስዋብ የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን በሚያደርጉበት ወቅት በዓሉን የማይመለከትና ሕግ የማይፈቅደውን ባንዲራ ለመስቀል ሙከራ ያደረጉ በመኖራቸው አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር” አልሸሸጉም፡፡

በተለይም ”ትላንት ታቦት በሚገባበት ወቅት አራተኛ በተባለው አካባቢ ተገቢ ያልሆነ ጭፈራና ንብረት ላይ ድንጋይ መወርወር መጀመሩን የአባይ ሚዲያ ምንጮች ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡