አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 13፣2012

በድሬዳዋ ከተማ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት ጎርጎሪዮስ የተባለውን ታቦት ለማስገባት ምዕመኑ በሚያጅብበት ሰዓት ታቦቱ እንዳያልፍ መንገድ ከዘጉ ቡድኖች ጋር በተደረገ ግጭት ፖሊስ ማረጋጋት ሲገባው ታቦት በማጀብ ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ ጥይት በመተኮስ ሰባት ሰዎችን መምታቱን የአይን እማኞች ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ  የተፈጠረውን  ግጭት  መንስኤ  እያጣራ እንደሆነ ገልፆ በአጠቃላይ በግጭቱ  የደረሰውን  ጉዳት  ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም 1 ሰው በድንጋይ ተመትቶ ሞቷል፣ 7 ሰው በጥይት ተመቷል፣ 2 መኪና በእሳት ተቃጥሏል፣ 2 መኪና  ተሰባብሯል፣ 1 የከብቶች መኖ መጋዘን በእሳት ተቃጥሏል ፣1 መኖሪያ ቤት በእሳት ተቃጥሏል፣ 14 የፖሊስ አባላት ላይ ድብደባ ተፈጽሟል፣3 መደብር ተዘርፏል ቁጥራቸው ያልተለየ መኖሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል ብሏል።

በስልክ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው መንገድ የዘጉ ግለሰቦችን ከቦታው አስወግዶ ታቦቱን ማስገባት እየተቻለ ጠብመንጃ ተኩሶ መግደል አልነበረበትም ይህም የድሬዳዋ ፖሊስ ጥፋት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ለድሬዳዋ ህዝብ እንዲህ አይነት እኩይ ተግባር አይገባውም የሚሉት ነዋሪዎቹ ከነበረው የተኩስ ክብደት የተነሳ ለመጀመሪያ ግዜ ታቦቱ ሩጦ ከሰው ግቢ በመግባት እና ምዕመኑ በመበተን የጎርጎሪዎስ ክብረ በዓል እክል ገጥሞት እንደነበር አስረድተዋል፡፡