አባይ ሚዲያ ዜና – ጥር 14፣2012

ከቀናት በፊት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር አቶ አድጎ የብልፅግና ፓርቲን ወክለው በመሄድ በወንበራ ከሚገኙ የጉምዝ ተወላጆች ጋር ውይይት ማድረጋቸውና በመድረክ ላይ አለመስማማት እንደነበር ተገልጧል።

አቶ አድጎ ወደ አሶሳ መመለሳቸውን ተከትሎ በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ የታጠቁ የጉምዝ ተወላጆች በአማራዎች ላይ ከጥር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በፈፀሙት ጥቃት 21 የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል ተብሏል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ኮማንደር አንዷለም እንየው ለአባይ ሚዲያ እንደገለጹት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላይ ክልሉን እየመራ ከሚገኘው ፓርቲ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ግድያ እንደፈጸሙ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው በየጊዜው በመቶዎች የሚቆጠር የጉምዝ ሚሊሻዎች እንደሚመረቁ በተለይ በጉባ ወረዳ አንጃኩያ ቀበሌ ወይም ባድጎሹ በሚባል አካባቢ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

ከሽናሻ ብሔረሰብ በህግ ተፈላጊ ናቸው የተባሉት የፓርቲ አመራር አቶ ለሜሳ ሰበታ ከህወሐት ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቆሙት ምንጮች በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱም ገልፀዋል።

ከሰሞኑ የጉምዝ ታጣቂዎች በንፁሀን አማራዎች ላይ ግድያ መፈፀማቸውን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት መግባቱ ቢነገርም በጉምዝ ታጣቂዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ አለመወሰዱን ክልሉ የጸጥታ ቢሮ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡