አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 15፣2012

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ብርሌ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበት የጎንደር የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ የሞከሩት በህወሓት የተላኩ ግለሰቦች ናቸው ብለዋል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ጥቃት ሊፈፀሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የላካቸው አካል ማንነትም ይፋ እንደሚደረግ ጠቁሞ ነበር።

ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ቤት እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት ሁለቱን ቡድኖች ያሰማራቸውን አካል ማንነት ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቆ ነበር፡፡

ኮማንደር ጌታቸው እንደሚሉት ለተጠርጣሪዎቹ ተልዕኮ የሰጣቸው ህወሃት ሲሆን የታቀደውም በትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ነው፡፡

እንደ ኮማንደሩ ገለፃ ተጠርጣሪዎቹ ብዛታቸው አምስት ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉትም ከጥምቀት ሶስት ቀን በፊት ማለትም ጥር 7/2012 ዓ.ም ነው፡፡

አንደኛው ቡድን ማለትም ሶስቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት በብሄራዊ መረጃና ደህንነትና በመከላከያ ትብብር ሲሆን የሌላኛው ቡድን ሁለት ተጠርጣሪዎች ደግሞ በልዩ ሀይልና በመከላከያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮማንደሩ አክለውም የተያዙት ተጠርጣሪዎች በዋናነት ሶስት ተልዕኮ ተሰቷቸው ነው የመጡት ያሉ ሲሆን አንደኛው ለዚህ ግዳጅ የሚተባበሩ መመልመል፣ሁለተኛው የጥምቀት በኣልን ማበላሸት ሲሆን ሌላኛው በበዓሉ ላይ የተገኙ አመራሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ተብሎ ታቅዶ ነው ብለዋል፡፡

እነማን እንደሆኑ ይታወቃሉ ስማቸውንም በምርመራው ሂደት የምንጠቅስ ይሆናል ያሉት ኮማንደሩ ተጨባጭ ማስረጃዎች መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኮማንደር ጌታቸው ከጠቀሱት ማስረጃዎች መካከልም በቂ የገንዘብ ዝውውር፣የጦር መሳሪያዎችና ፈንጂዎች ይገኙበታል፡፡

አካሄዳቸው በጣም የተወሳሰበ አይደለም ግልፅ ነው ያሉት ኮማንደር ጌታቸው ሁሉንም ነገር ምርመራው በሰፊው አጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ኮማንደሩ ምርመራውን ለክልል መንግስት አስረክበናል የፌደራል መንግስትም ይገባበታል ያሉ ሲሆን ጥቃቱ ኢላማ ያደረጋቸው አመራሮችም እነማን እንደሆኑ በምርመራው እንደሚገለፅ መናገራቸውን የአሜሪካን ድምጽ ዘግቧል፡፡