አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 15፣2012

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ህዝቡ በነገው እለት በሁሉም የምርጫ ክልሎች በሚደረገው የአስፈፃሚዎች ምርጫ በንቃት እንዲሳተፍ ሲል ለከተማው ነዋሪ ጥሪ አቅርቧል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ባሳወቀው መሰረት ነገ ጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም የአስፈፃሚዎች ምርጫ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ይካሄዳል ብሏል።

የአስፈፃሚዎች ወይም የታዛቢዎችን ምርጫ የሚያካሂደው የምርጫ ቦርድ መሆኑን የገለፀው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ታዛቢዎች ገለልተኛና በጥንቃቄ የተመረጡ ሊሆኑ ይገባል ሲል አሳስቧል።

ባልደራስ እንደገለፀው ባለፉት አምስት የምርጫ ዘመናት ኢህአዴግ ሲፈፅመው በነበረው የምርጫ ኮሮጆ ግልበጣ በወንጀል ድርጊቱ ከተሳተፉት መካከል የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደሚጠቀሱ አውስቷል።

ኢህአዴግ አደረኩት በሚለው ምርጫም በምርጫ አስፈፃሚነት ሲቀርቡ የነበሩት ገለልተኛ ሳይሆኑ ይልቁንስ የገዥው ፓርቲ አባላት፣ የሊግ፣ የወጣት፣ የሴቶችና የፎረም አባላት እንደነበሩ በማውሳት በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያጡ እንደነበር ነው ባልደራስ የገለፀው።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሲቀጥል ባለፉት የምርጫ ዘመናት በህዝብ ላይ የተፈፀሙት ሕገ ወጥና ፀረ ዲሞክራሲያዊ አካሄዶች እንዲደገሙ አይፈልግም ብሏል በመግለጫው።

ፓርቲው በአዲስ አበባ በሚካሄዱት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለእውነት እና ለእውነት ብቻ የቆሙ የምርጫ አስፈፃሚዎችንና ታዛቢዎችን በመምረጥ ሂደቱ ህዝቡ በንቃት መሳተፍ አለበት ብሏል።

በመሆኑም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በነገው እለት በምርጮ ቦርድ መሪነት በሁሉም የምርጫ ክልሎች በሚደረገው የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ የአዲስ አበባ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ነው ጥሪውን ያስተላለፈው።