ሀረር እና ስጋቶቼ (በወንድማገኘሁ አዲስ)

ከ15 ወራት በፊት ሀረርም ድሬዳዋም ሆኜ ከተሞቹ አደጋ ላይ እንደሆኑ በፌቡ ደጋግሜ ስፅፍ ነበር። ሀረርን የቆሻሻ ክምር ውጧት ፣ ተረኞች ጡንቻቸውን መሀል አስፋልት ላይ የሚያሳዩበት ሆና፣ ድሬዳዋ ላይ “የመጤዎች ልቀቁ” ቀለም በየበሩ እየተቀባ የነበረበት ወቅት ላይ እዚያ ነበርኩ። ዛሬ ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገሩቱ ባለ አዞ እምባዎች ያኔ አትዋሽ፣ አታካብድክ፣ መአት አትጥራ ሲሉኝ ነበር።
ከዛም በኋላ ቢሆን መከታተሌን አላቆምኩም። እስከ ሰሞኑ ድርጊት ድረስ በርካታ አሰቃቂ ድርጊቶች ተፈፅመዋል። ሰሞኑን የጃዋር- መራራው ኦፌኮ የዘንድሮውን ጥምቀት የደም ጎርፍ የሚናኝበት፣ ታላቅ ሀገራዊ ቀውስ የሚከሰትበት እንዲሆን ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ የሚጮሁ የቀበሮ ባህታዊያኑን አሰልፎ ያላደረገው ጥረት የለም። አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም በዋናነት በፈጣሪ ምህረት ሲቀጥልም በህዝቡ አርቆ አስተዋይነትና ትግስት ሴራው ከሽፏል ባይ ነኝ፣ ከሽፏል ስል መክኗል እያልኩ አይደለም።
በተለይም የኦፌኮ አመራሮችን እና OMN ን  ሀይ ባይ እንደሌላቸው ሳስብ የአደጋው ቀጣይነት እና አስከፊነት ፍንትው ብሎ ይታየኛል። የሁለቱን ሰሞኑን ስላነሳሁት ሌሎች የሚያሳስቡኝን አንድ 4 ነገሮች  ላንሳ።
1- የክልሉ መንግስት ፀጥታ ሀይል ገለልተኛም/ተአማኒም አለመሆን እና አቅመቢስነት
#ኡስታዝ አህመዲን ጀበል እንደነገሩንና እንዳስነበበቡን ከሀረሪ ክልል ፖሊስ ጋ እንደተገናኙ፣ ይፈጠራል ተብሎ በተፈራው ችግር ዙሪያ መፍትሄ አፈላላጊ ከነበሩት  አካላት ውስጥ የኦርቶዶክስ እምነት ተወካዮች በመጨረሻው ስብሰባ እንዳልተገኙ እና ጭራሽ ስልኮቻቸውን እንደዘጉ፣ በአካባቢው ያሉ ፅንፈኞች ከአደጋ እንዲታቀቡ ለሳቸው እና ለጃዋር ተከታዮቻቸውን በማህበራዊ ሜዲያ እንዲያሳስቡ እንደተነገራቸው ገልፀውልናል።
#ይህ የሚያሳየን የክልሉ ፖሊስ የአካባቢውን ሰላም የማረጋገጥ አቅሙ ወይ ደካማ መሆኑን አሊያም ለአካባቢው ደህንነት መጠበቅ የተጠቀሱት ሰዎች “መልካም ፈቃድ” የግድ መሆኑን ነው። ሲጀመር ችግሩ በማን ተፈጠረና ነው ጃዋር ለመፍትሄው የታጨው? ይሄ ሰው በምንስ አግባብ ነው በሀረሪ ክልል የፀጥታ ጉዳይ እጁን እንዲያገባ የተፈቀደለት? ** በነገራችን ላይ ይህ የክልል ፖሊስ  ላለፉት 29 አመታት አማርኛ ተናጋሪ በሆነው ሰፊ የማህበሰብ ክፍል ላይ ምን ምን በደሎችን ይፈፅም እንደነበረ አስፈላጊ ከሆነ መዘርዘር ይቻላል። ከለውጡ በኋላ ባለው ሁኔታ ደሞ የሀረሪ ፖሊስ የአካባቢውን ፅንፈኞች ምን ያህል እንደሚፈራቸው ባይኖቼ አይቻለሁ። መሳሪያውን አንከርፍፎ በባለ ሁለት ሞባይሎቹ፣ ባጎፈሩትና አይኖቻቸውን በሚያጉረጠርጡት ፅንፈኛ ጎረምሶች ፊት እንዴት እንደሚርድ እና እንደሚርበተበት ሀረርን ለቀናት የጎበኘ ሁሉ ምስክር መሆን ይችላል።
2- የመንግስት ዳተኝነት ወይም የህገመንገስቱ ማነቆነት
የፌደራል መንግስት ችግሩን በሚገባ ያውቀዋል።  ሀማሬሳና ቀላድ/ክብሪት አምባ ያሉት በርካታ የመከላከያ ካምፖች  ችግሩ ከተፈጠረበት ቦታ እጅግ በቅርበት ነው የሚገኙት። ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታቱን ለጊዜው እንተወውና የተከሰቱት ችግሮች እንደሚደርሱ አስቀድሞ እየታወቀ እና በዋዜማው ትልልቅ ምልክቶች እየታዩ እንዴት መከላከያ እና ፌዴራል ፖሊስ ላይደርሱ ቻሉ? ክልሉ ስላልጠየቀም ሊሆን ይችላል! ማን ያውቃል የጃዋር ፈቃድ ያስፈልግም ይሆናል!
3- የአህመዲን ጀበል ላይቭ ንግግር
ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ከሚያደንቁ፣ ከሚያከብሩ፣ በታሰሩበት ጊዜም ካለማቋረጥ ድምፅ ከሆኑት ሰዎች አንዱ ነኝ። ግን ከፖሊስ አባሉ አገኘሁት የሚሉትን መረጃ ብቻ ይዞ ከኦርቶዶክስ እምነት ተወካዮች ሳያረጋግጡ ተወካዮቹን ለመፈረጅ መቻኮላቸው ለምን አስፈለገ?  በእስልምና ተቋማት ላይ የተደረጉትን ጥቃቶች በፅንፈኞች እንደተፈፀሙ ገልፀው በአብያተክርስቲያናት ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች “ፖለቲካዊ ጥቃቶች ናቸው” ሲሉ መፈረጃቸውን ከማከብራቸው ኡስታዝ ባልሰማው ትንሽ ይቀለኝ ነበር።  ኦሮሚያ ውስጥ በበርካታ ካህናት ምእመናን እና አብያተክርስቲያናት ላይ የተፈፀመውን ግፍም ኡስታዝ እንዳላዩ አልፈውታል ። እንዲሁም ባንዲራዋን የያዙትን “የእምነትና የብሄረሰብ መብትን ያለመቀበል መብታቸው ነው” በማለት ያስተላለፉት መልክት ሌላው ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነበር። ለዚች ሰንደቅ ፍቅር ያላቸው ዜጎች “የብሄር ወይም የእምነት ብዝሀነትን የማይቀበሉ ናቸው” የሚል ፍረጃ አደገኛ ነው። እቺን ባንዲራ እያውለበለቡ ለኡስታዝም ሆነ ለሙስሊሞቾ መብቶች መከበር ክርስቲያንና ሙስሊም ኢትዮጲያዊያን ባለም ዙሪያ ከፍተኛ ትግል ለአመታት ማድረጋቸው ሊሰመርበት ይገባል። ሀውልት በማፍረስ ዙሪያ፣ እንዲሁም ሙስሊሞች እና ንብረታቸው የጥቃት ሰለባ ሆነዋል ብለው በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውንና በበርካታ ማስረጃዎች የተደገፈውን ሀቅ መግደፋቸውም እጅግ አሳዝኖኛል። ከየ ድርጊቱ በኋላ በብርሀን ፍጥነት ነፃ የምርመራ ሂደቶችን አቅጣጫ ለማስቀየር የሚደረጉ ንግግሮችና መግለጫዎች ሊታሰብባቸው ይገባል ባይ ነኝ። ገጀራና ዱላ ይዞ መንገድ ሊዘጋ ለወጣ የነውጠኛ መንጋ የማርያም መንገድ ማፈላለግ ከአንድ የተከበረ የሀይማኖት መምህር እና መሪ የሚጠበቅ አይደለም።
4- የኢኦቤክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ የሰጡት መግለጫ
#አባ በንግግራቸው የተፈጠረውን እንዳልሰሙ ገልፀዋል። በበኩሌ ይህ አባባል አልተመቸኝም። በመላው ሀገሪቱ ያለውን የእምነቱን አባላት እና ተቋማት ደህንነት የመከታተል ሀላፊነት በዋነኝነት የቤተክህነት ነው። ቢያንስ ማህበረሰቡን ማረጋጋት፣ ድርጊቱ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ መወትወትና ምርመራውን በቅርብ ርቀት መከታተል የኢኦቤክ ግዴታና ሀላፊነት ይመስለኛል። ከዋናው ቤተክህነት ይልቅ አባ መቃሪዎስ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፍፁም ሀላፊነት የተሞላበትና ሸፍጥ ያልታከለበት ነበር። ምንም እንኳን ኡስታዝ የኦርቶዶክስ ተወካዮች ራሳቸውን እንዳገለሉ ቢገልፁም ፖሊስ እንዴት ሊሰማቸው፣ ሊተባበራቸው እንዳልፈለገና ብሎም እንደተኮሰባቸው በግልፅ አማርኛ አብራርተውታል።
በመጨረሻም በሀረርና በድሬዳዋ ከተሞች እየተፈፀመ ያለው ግፍ በዚህ ከቀጠለ መዘዙ ሀገራዊ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። የሀረሪ ክልል መለያው ፀረ ክርስትናና ፀረ አማርኛ ተናጋሪ መሆኑ ላለፉት በርካታ አመታት በተግባር የተፈተሸ ነው። የሀረርን ተምሳሌታዊ እሴቶች ቅርጥፍ አድርጎ የበላው ክልሉን እያስተዳደረ/እያቆረቆዘ ያለው የሀረሪ ክልል መንግስት ራሱ ነው። የፍቅርና የመቻቻል ባህሏን በዙሪያው ከሚገኙ ፅንፈኞች ጋ በማበር ሲያደበዝዝ የነበረ አሁንም ለውጥ የሚባለው ሂደት ያልነካካው ይህ ክልላዊ መንግስት ነው። በመተቃቀፍ ያደግንባት፣ ምሳሌ ሆነን ሀገር እስኪመሰክርልን ድረስ የፍቅር ተምሳሌቶች የተባልንባት ሀረር ዛሬ ዘመን ያገነናቸው ባለሜንጫዎች የሚፈነጩባት ጥላቻ የሚዘራባትና የሚታጨድባት ከተማ ሆናለች። በርካቶች ተወልደው ያደጉባትን፣ ድረው የኳሉባትን ሀረር እየለቀቁ ነው። ሀረሬነት ሊያብብ ሊጎመራና እንደ ሀረግ ሊሰፋ ሲገባው ዘረኝነት ባንሰራፋው አረም ታንቆ እየጠወለገ ነው። መንግስት እንደ መንግስት የሀይማኖት መሪዎችም እንደ ሀይማኖት መሪዎች መሆን ካልቻሉ የማይቀለበሰው አደጋ ቅርብ ነው። የሚና መደበላለቅ ሀገር እያፈረሰ ነው።  የፖለቲካ የሜዲያ ድርጅቶችና አክቲቪስት ተብየዎች ህጋዊ ልጓም ሊጠልቅላቸው ይገባል። ችግሮችን ማሳደር እንዲራቡ የመፍቀድ ያክል ነውና መንግስት ሀላፊነቱንና ግዴታውን ጊዜ ሳይወድ እንዲወጣ ሁላችንም ግፊት ማድረግ ይጠበቅብናል።
ፈጣሪ ኢትዮጲያን አብዝቶ ይባርክ!!