አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 17፣2012

በአማራ ክልል ከተሞች በመጭው ማክሰኞ ሊካሄድ የታሰበው ሰልፍ በኦሮሚያ ክልል የታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ አማራ ተማሪዎች እንዲፈቱ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጧል፡፡

ከታገቱ ሳምንታትን ያስቆጠሩትን የአማራ ተወላጅ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እስካሁን ያሉበት ባለመታወቁ ተማሪዎች እንዲለቀቁ ጫና ለመፍጠር የሰላማዊ ሰልፍና የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት እንደሚደረግ አባይ ሚዲያ ያነጋገራቸው የአማራ ወጣቶች ማህበር  የወልዲያ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኤፍሬም አሰፋ ገልጸውልናል፡፡

መንግስት ሀላፊነቱን እየተወጣ አይደለም የሚሉት የወጣት ማህበራቱ የአማራን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲያስጠብቅ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለማስተላለፍ መታቀዱንም ኤፍሬም አሰፋ ገልጸውልናል፡፡

በተመሳሳይ ዓሲምባ ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም በመላው የአማራ ከተሞች በኦሮሞ ፅንፈኞች “የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ” ድምፅ ለመሆን የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ እደግፈዋለሁ ብሏል።

ዓሲምባ እንዳለው በአማራ የተለያዩ ከተሞች በአስተባባሪዎች ታግዞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ይደረጋል የተባለው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተገቢ መሆኑን አምኖበታል።

ጉዳዩም አንድ ወገንን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ልጅና እህት ያለው ስለእናቱ ብሎ ድምፅ የሚያሰማበት ቀን መሆኑን ስለምናምን፣ እኛም ከጎናችሁ መሆናችንን እንገልፃለን ሲል ነው ዓሲምባ ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በይፋዊ ገፁ ያስታወቀው።

በአሁኑ ሰዓትም በሁሉም የክልሉ ከተሞች የሚገኙ የአማራ ወጣቶች ማህበር አመራሮችና ወጣቶች በሰልፉና በሻማ ማብራት ስነ ስርዓቱ ላይ ስለሚደረጉ ሁኔታዎች ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ውይይት ላይ እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡