አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 17፣2012

ከዘጠኝ ወራት በፊት የተመሠረተው የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ም/ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠየቀውን የፋይናንስ ድጋፍ ባለማግኘቱ የሚጠበቅበትን ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉን ጠቁሞ፣ ከዚህ በኋላ በአባላቱ መዋጮ ራሱን ለማጠናከር መወሰኑን አስታወቀ፡፡

ሰሞኑን የጋራ ም/ቤቱ ከተቋቋመ ወዲህ ያከናወናቸውን ተግባራት ለአባላቱ፤ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሰጠው ጠይቆት የነበረውን የ3.8 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት አለመቻሉን የም/ቤቱ ም/ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ም/ቤቱ በፓርቲዎች የቃል ኪዳን ስምምነት መሠረት፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋፍ ሊያደረግለት ተስማምቶ የተቋቋመ ቢሆንም፤ ምርጫ ቦርድ የሚፈለገውን ድጋፍ ባለማድረጉ ለውስን አባላት ስልጠና ከመስጠትና ከ30 የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የስራ ግንኙነት ከመፍጠር የዘለለ ተግባር አለማከናወኑን አቶ ግርማ አስረድተዋል::

ከምርጫ ቦርድ የሚፈለገው የ3.8 ሚሊዮን ብር የስራ ማስኬጃ ድጋፍ አለማግኘቱን ተከትሎ በአባላቱ መዋጮና ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለማፈላለግ መወሰኑን ም/ሰብሳቢው ገልፀዋል፡፡

ም/ቤቱ የፋይናንስ አቅሙን ካጐለበተ በኋላም በቀጣይ በዋናነት በፓርቲዎች መካከል ያለን የእርስ በእርስ ቅራኔ ለመፍታት እንደሚሠራና ሌሎች እቅዶችንም ነድፎ እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ ተችሏል፡፡