አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 18፣2012

በደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ “በነያ ቀበሌ” ከ2 ወር በፊት 12 ንጹሃን በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ስለመገደላቸው እና መረጃው ከአካባቢው ህብረተሰብ እንዳይወጣ መደረጉን የጋሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ዘግቧል፡፡

አርሶ አደሮቹ የተገደሉት “የኦነግ ታጣቂዎች” ናቸው በሚል የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኋላም ሟቾቹ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ ከሚታመነው የታጠቀ ሀይል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው የአካባቢው ተወላጅ አርሶአደሮች ስለመሆናቸው መረጋገጡ ተገልጿል።

ይሄ መረጃ ከአካባቢው መውጣት እንደሌለበት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ማስፈራርያ እንደደረሰባቸው፤ ከዝያም በላይ የሟቾቹን አስክሬን እንዳይቀብሩ ስለመከልከላቸው መረጃውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

መረጃው ከደረሰበት ዕለት አንስቶ እውነታነቱን ለማረጋገጥ ባደረገነው ጥረት ጉዳዩ እስከ ክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ድረስ እንደሚታወቅ እና መረጃው እንዳይወጣ እንደተፈለገ ለማረጋገጥ ተችሏል።

ሥማቸው ለደህንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰብ እንዳረጋገጡት ከሆነ “ግድያውን የፈጸሙት በአካባቢው በጋራ የሚንቀሳቀሱት መከላከያ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የቡርጂ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አባላት ሲሆኑ የአርሶ አደሮቹን አገዳደል በተመለከተ በአንድ ሥፍራ ላይ እንዲሰባሰቡ ካደረጓቸው በኋላ በደረታቸው አስተኝተው አውቶማትክ ጥይት በላያቸው ላይ በማዝነብ ረሽኗቸዋል“ በማለት ገልፀዋል።

“የሟቾች አስክሬን እንዳይነሳ በመከልከሉ አብዛኞቹ በአሞራና ጅብ ተበልተዋል” በሚል የገለጹልን የአካባቢው ነዋሪዎች አስክሬኖቹ በአንድ ላይ ተከማችተው የሚያሳይ ተንቀሳቀሽ ምስል ለጂ ኤም ኤን አድርሰውኛል ብሏል በዘገባው።

የሟቾቹ የሥም ዝርዝርም፡- ኃይለማሪያም ዘበኛ፣ ገሤሤ ገብሬ፣ ወንድሙ ቡምጳ፣ ሳንች ዳንኤል፣ ሲሣይ በዙ፣ ታሪኩ ገብረሀና፣ ወይሬ ቦጋሌ ለሥራ በአከባቢው የነበሩ 2 የደራሼ፣ 2 የአሌ እና 1 የኮንሶ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡

ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ”በአንድ ማግስት በቀበሌያችን የተፈፀመውን ግፍ የዓለም መንግሥት ይስማልን እንዲሁም ሰብአዊ መብትና ዕንባ ጠባቂ ይምጣልን ማለታቸውን የዘገበው የጋሞ ሚዲያ ኔትወርክ ነው፡፡