አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 18፣2012

በሀረሪ ክልል በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ተፈጥሮ ከነበረው ሁከት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ 87 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

ከበአሉ አከባበር ጋር የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከሐይማኖትም ሆነ ከብሔር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ቢሮ አያይዞ ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ናስር ዩያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ባሳለፍነው ሳምንት ከጥምቀት በአል አከባበር ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት በፈጠሩት የፀጥታ ችግር ምክንያትም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የ11 ህንፃዎች መስታወት የተሰባበረ ሲሆን አንድ የኮካኮላ ማከፋፈያና አንድ ተጨማሪ ህንፃ መቃጠላቸውን ገልጸዋል ።

ሁለት መኪኖች እና አራት ባጃጆች ጭምር በሀከቱ መቃጠላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል ።

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገ ሲሆን 63 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት ተጀምሯል ።

እንደ አቶ ናስር ገለፃ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጥቂት ነዋሪዎች በስጋት ቀያቸውን ለቀው ሔደው የነበረ  ቢሆንም በአፋጣኝ እንዲመለሱ ተደርጓል ።

የተፈጠረው ሁከትና የፀጥታ ችግር ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት የክልሉ ነዋሪ በሰላም ፣ በመቻቻልና በአንድነት የመኖር እሴት ለመሸርሸር ያሴሩት የጥፋት አጀንዳ መሆኑን ጠቁመው ከሐይማኖት እና ከብሔር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንፃራዊ ሰላም እየታየ መሆኑን ያመላከቱት የቢሮው ሀላፊ በክልሉ ከሚገኙ የሐይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣አባገዳዎች፣ወጣቶችና ቄሮዎች እንዲሁም ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት የክልሉን ሰላም ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።