አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 18፣2012

ከኦሮሚያ ክልል ከፈንታሌ ወረዳ አልጌ ቀበሌ ተፈናቅለው በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትኩረት እንደነፈጓቸው ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል መተሀራ ከፈንታሌ ወረዳ አልጌ ቀበሌ ከህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ  በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

ለዘመናት ከሚኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የሆኑ ዜጎች በወቅቱ በናዝሬት፣በአዋሽ ሰባትና በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ መጠለላቸውም ይታወቃል።

በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ከተጠለሉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መካከል ከተጠለልንበት ጥቃት ሊያደርሱብን የሚችሉ ፅንፈኞች አሉ በሚል በደህንነት ስጋት 149 የሚሆኑት ወደ ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ከተማ ከመጡ 10 ወራትን አስቆጥረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ እና የአማራ ክልል መንግስት እያደረገላቸው ላለው እገዛ ምስጋና ያቀረቡት ዜጎች የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግስት ትኩረት የነፈጓቸው መሆኑን በማውሳት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

በፈንታሌ አልጌ ቀበሌ ብቻ ከ2008 ጀምሮ በአካባቢው ባሉ በተደራጁ የአካባቢ ወጣቶችና ጥቃት አድራሾች አማካኝነት እንደተገደሉ ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

በ2011 ዓ.ም ፅንፈኞች የአማራ ተወላጆችን በማፈናቀል 150 የሚሆኑ የመኖሪያ ቤቶችን የቀበሌ አመራሮች ባሉበት ተከፋፍለው እንደነበር አስተያየታቸውን የሰጡ ተፈናቃዮች አስረድተዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም ከአልጌ ቀበሌ ከተፈናቀሉት መካከል 127 የሚሆኑ አባዎራዎች በናዝሬት፣በአዋሽ ሰባት እና በአረርቲ የሚገኙ ሲሆን እስካሁን ወደነበሩበት ቀዬ አለመመለሳቸው ተነግሯል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲቀጥሉ በአሁኑ ስዓት ግብር እየከፈልንበት ባለው መሬት ተጠቃሚ የሆኑት የከረዩ እና የኢቲ ብሄረሰቦች የእኛን ማሳ ይገባኛል አይገባኝም በሚል ምክንያት እየተጋጩበት ይገኛሉ ብለዋል።

በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የአካባቢው መስተዳድር አካላት ተመልሰን እንድንገባ ባለመፈለጋቸው እስካሁን ወደ ቀያችን እንድንመለስ አልተደረገም ያሉት ተፈናቃዮች በአሁኑ ስዓት 40 የሚሆኑ አባዎራዎች በአረርቲ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአንድ ክፍል ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ መግለጻቸውን የአማራ ሚዲያ ማእከል።