አባይ ሚዲያ ዜና- ጥር 18፣2012

ኢትዮጵያን ከጎሳ ወደ ኃይማኖት ግጭት እየወሰዳት ያለው የቅርብ ጊዜ አካሄድ ብዙዎችን አስፈርቷል፡፡

በአብዛኛዉ በፖለቲካ ጥቅም ሽሚያ የሚገፋዉ የኢትዮጵያ የጎሳ ጠብና ግጭት ባለፈዉ ዓመት ከመንፈቅ ወዲህ ሺዎች እንዲገደሉ፣ ሚሊዮኖችን እንዲፈናቀሉና አንዲሰደዱ ማድረጉ አነጋግሮ ሳያበቃ፣ የነባሮቹ የኢትዮጵያ ኃይማኖቶች ተከታዮች እንዲጋጩ፣ የኃይማኖት ተቋማትን እንዲቃጠሉ፣ ሱቆችና የንግድ መደብሮችን እንዲነዱ፣ እንዲወድሙና እንዲመዘበሩ ማድረጉ የሀገሪቷን የህልውና እጣፈንታ አስጊ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ከጂጂጋ እስከ እስቴ፣ ከሞጣ እስከ ሐረር በሙስሊምና በኦርቶዶክስ ክርስቲያን ስም የተነሱ ኃይላት በድምሩ በመቶ የሚቆጠሩ መሳጅድና አብያተ ክርስቲያናትን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አቃጥለዋል።

በብዙ ዓመታት ልፋትና ጥረት፣ በብድርና ልቆ የተቋቋሙ፣ ሱቆች፤ ሆቴሌች፣ ሻይና ምግብ ቤቶች፣አገልግሎት መስጪያ መደብሮችን  አጋይተዋል።

የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር በክልሉ የተነሱ የጥፋት ኃይሎችን ፈጥኖ መቆጣጠሩ፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ጉዳት የደረሰባቸዉን ምዕመናን መደጎሙን መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።

የኦሮምያ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድርም መስተዳድራቸዉ በክልሉ በሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥፋቶችን እንደሚቆጣጠር ባለፈዉ መስከረም ቃል መግባታቸዉን ሰምተናል።

ከዚሕ ዉጪ በተለይ ሞጣ ዉስጥ መሳጅድና የሙስሊሞች የንግድ ተቋማት ከወደሙ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት የሚሰነዘርበት የአማራ መስተዳድር እስካሁን አጥፊዎችን ያልተቆጣጠረበትን ምክንያትም ሆነ፣ ተመሳሳይ ጥፋቶችን ለመቆጣጠር መዘጋጀቱን መፈለጉንም በግልፅ አላስታወቀም በሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።

የሌሎች ክልሎች መስዳድሮች፣ የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎችም ግጭቶችና ጥፋቶችን ለማስቆም አልጣሩም ተብለዉ በሰፊዉ እየተወቀሱ ነዉ።

ቅሬታ፤ ወቀሳና ትችቱ የፖለቲካና የፀጥታ ባለስልጣናት ራሳቸዉ የግጭቱ አካል ናቸዉ የሚል ጥያቄና ጥርጣሬ እያጫረ ነዉ።

የአንዱ ወይም የሌላዉ ኃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች ግጭቱ እንዲባባስ የሚደርጉት ቅስቀሳ፣ ዛቻና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩት ስድብ፣ ጠብ ጫሪ መልዕክት እንደቀጠለ መሆኑ በሌሎች ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እየተናጠች ያለችውን ኢትዮጵያ ጥፋት ያፋጥናል የሚል ስጋት አምጥቷል።

አባይ ሚዲያ በዚህ ስጋት ዙሪያ በተለይም ከእስልምናና ከኦርቶዶስ የሀይማኖት መምህራን ጋር ቆይታ በማድረግ የተዘጋጀውን ልዩ ዘገባ በዩቲዩብ ቻናላችን እንድትከታተሉት  እንጋብዛለን፡፡