አባይ ሚዲያ ዜና -ጥር 19፣2012

የዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ በተለይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊ የሆኑ 75 ሰዎች በሳምንቱ መጨረሻ በጅምላ ተስረዋል፤ በአስቸኳይ ይፈቱ ሲል አሳስቧል።

ደጋፊዎቹ የታሰሩት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ነው ያለው መግለጫው በተለይም በምዕራብ ጉጂ ዞን ፊንጫ ከተማ እንዲሁም በሻምቡ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ተጠቅሰዋል።

ጋብ ብሎ የነበረው የመብት ተቆርቋሪዎች፣ የተቃዋሚዎችና የፓርቲ ደጋፊዎች የጅምላ እስር እየተመለሰ እንደሆነ ምልክቶችን እያየን ነው፤ ይህ ደግሞ ያሳስበናል ብሏል በመግለጫው።

“ይህ ድንገቴ የጀምላ እስር የዲሞክራሲ መብቶችን ሚሸረሽር ነው፤ በተለይም ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን በሚጠበቀው የመጪው ምርጫ ላይ ጥላውን ያጠላል” ብለዋል የአምነስቲ ኢንርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዲፕሮሴ ሙቼና።

ከታሳሪዎቹ መካከል ጫልቱ ታከለ ትገኝበታለች። ፖሊስ የጫልቱ ቤተሰቦች ይኖሩበታል ተብሎ በሚገመተውና ሻምቡ በሚገኘው መኖርያ ቤት እሁድ ጥር 17 ሌሊት 11 ሰአት ሰብሮ በመግባት በቁጥጥር ሥር አውሏታል ብሏል መግለጫው። አሁን በሻምቡ ፖሊስ ጣቢያ እንደምትገኝም ገልጿል።

ጫልቱ በፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ‘የአሸባሪው’ የኦነግ አባል ናት በሚል ለስምንት ዓመታት በእስር ማሳለፏን የጠቀሰው መግለጫው፤ ኦነግ ከአሸባሪ ድርጅትነት በመሰረዙ ለውጦች ታይተው ነበር ብሏል።

ሆኖም ጫልቱ በድጋሚ 2017 ለአጭር ጊዜ መታሰሯን በኋላም በ2019 እርጉዝ ሳለች በድጋሚ መታሰሯን ያወሳል።

ባለፉት የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የተካሄዱት የጅምላ እስሮች ያሳሰቡት አምነስቲ ፖሊስና መከላከያ የመልሶ ማቋቋሚያ ስልጠና በሚል ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ እስር ሲያካሄድ ነበር ሲል ይከሳል።

ሆኖም ብዙዎች በተለያዩ የመከላከያና የፖሊስ ማጎሪያዎች ጊዜያቸውን ካሳለፉ በኋላ በመስከረምና ጥቅምት ወር ላይ መፈታታቸውን ያስታውሳል፤ መግለጫው።